የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ትርጉም ያለው ለውጥ እያስገኘ ነው – አብርሃም በላይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመስኖና ቆላማ አከባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በማህበረሰቡ ህይወት ውስጥ ትርጉም ያለው ለውጥ እያስገኘ ነው አሉ።
በአፋር ክልል የተተገበሩ የአርብቶ አደሮች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክቶች በዛሬው ዕለት ተመርቀዋል።
ሚኒስትሩ ከአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ጋር በመሆን በክልሉ በቆላማ አከባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት የተሠሩ የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ሚኒስቴሩ በተለያዩ ክልሎች ቆላማ አከባቢ በሚተገብራቸው የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክቶች የዜጎችን ህይወት በቀጥታ ማሻሻል ችሏል።
የፕሮጀክቱ ዓላማ በቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ ህይወት ለማሻሻል የሚያግዙ ተግባራትን ማጠናከር መሆኑን ጠቅሰው÷ የአፋር ክልልም ፕሮጀክቱ በስፋት ተግባራዊ ከሚደረግባቸው አካባቢዎች አንደኛው መሆኑን ተናግረዋል።
በድጎማ ሳይሆን በራሱ በጀት ማህበረሰቡን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ስራ መገባቱንና ውጤትም እየተገኘበት እንደሚገኝ አንስተዋል።
ለሕዝባችን ቅርብ ነን ስንል በምክንያት ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ ለዚህም ከዚህ ቀደም በአርብቶ አደርነት ብቻ የሚታወቀውን ማህበረሰብ በተሠሩ የመስኖ ፕሮጀክቶች በዓመት 3 ጊዜ በማረት ህይወቱን እንዲቀይር ማድረረግ መቻሉን አመልክተዋል።
በምንተስኖት ሙሉጌታ