Fana: At a Speed of Life!

የስታትስቲክስ ዘርፉ በግብርና ቆጠራ፣ በስነ ሕዝብና ጤና ጥናት ተጨባጭ ውጤት አስመዝግቧል – አቶ አብዱልአዚዝ ሸፋ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ የስታቲስቲክስ ዘርፍ ልማት የግብርና ቆጠራን፣ የስነ-ሕዝብና ጤና ጥናትን ዘመናዊ ለማድረግ ያስቻለ ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል አለ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፡፡

”የመረጃ ሉዓላዊነት ለፖሊሲ ነጻነት” በሚል መሪ ሀሳብ ኢትዮጵያ በመረጃና በስታቲስቲክስ የሉዓላዊነት ጉዞ ባስመዘገበችው ስኬት ላይ ያተኮረ ሀገራዊ ጉባኤ ተካሂዷል።

በኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት የኢኮኖሚ ስታቲስቲክስ ዘርፍ ኃላፊ አብዱልአዚዝ ሸፋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ የስታቲስቲክስ ልማት ፕሮግራም ዋና አላማ መንግስት ለሚያከናውናቸው ተግባራት አስፈላጊ መረጃዎችን ማምረት ነው፡፡

በዚህም ከባለድርሻ አካላት ጋር በሚያስፈልጋቸው መረጃ ዙሪያ ጽንሰ ሀሳብ ከማደራጀት እስከ ውጤት ድረስ በእቅድ፣ በቅንጅትና ባልተበጣጠሰ አሰራር በጋራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በቤተሰብ፣ በድርጅትና በወርሃዊ ደረጃ የሚከናወኑ ጥናቶች መኖራቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፥ በየወሩ የሚከናወነው የሸማቾች ዋጋ ጥናት የኢኮኖሚ ሁኔታ የሚለይበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጥናቱ እስከ 95 በመቶ የማረጋገጫ ሁኔታንና የተለያዩ ሳይንሳዊ ዘዴዎችን በመጠቀም ይከናወናል ነው ያሉት፡፡

በተቋሙ በየሦስት ወር የሚጠና የስራ ስምሪት ሁኔታ፣ ዓመታዊ የግብርና ናሙና ጥናት እንዲሁም በየአምስት አመት የሚከናወኑ የስነ ሕዝብ እና ጤና ጥናቶች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የሰብል፣ የቤት እንስሳት፣ የአካባቢ እንዲሁም የከተማና የገጠር ስታቲስቲክስ መኖራቸውን ያነሱት ኃላፊው፥ በእነዚህ አሰራሮች መሰረት መረጃን በከፍተኛ ሁኔታ ማሰበሰብ መቻሉን አመልክተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በጤና እና ግብርና ስራዎች ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን በተደረገው ጥናት መረጋገጡንም አንስተዋል፡፡

አሁን ያለውን የስታቲስቲክስ መሰረተልማት በማዘመን ወደ ግዙፍ ዳታ መሻገር እንዲሁም የሳተላይት ምልከታዎችን በራስ አቅም ማከናወን ተቋሙ በቀጣይ በትኩረት ከሚሰራባቸው ዘርፎች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአቤል ነዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.