መንግሥት የማኅበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻል በቁርጠኝነት እየሰራ ነው- አቶ አወል አርባ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት የማኅበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻል በልዩ ትኩረትና ቁርጠኝነት እየሰራ ነው አሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ጋር በመሆን በክልሉ ገቢ ረሱ ዞን ዱለቻና አሚበራ ወረዳዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
አቶ አወል አርባ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ክልሉ ሰፊ የአርብቶ አደር ማኅበረሰብ የያዘ በመሆኑ የማኅበረሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻል መንግሥት በልዩ ትኩረትና ቁርጠኝነት እየሰራ ነው።
በዛሬው ዕለት የተመረቁ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ተደራሽነትን ከማስፋታቸው ባለፈ ለማኅበረሰቡ ጤናማ ሕይወት መረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል።
በተለይም ሴቶችና ሕፃናት የነበረባቸውን የውሃ ፍለጋ እንግልት በማቃለል ትልቅ እፎይታ የሰጡና የሕፃናትን የትምህርት ጊዜ በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
ፕሮጀክቶቹ የክልሉ አርብቶ አደሮች ንጹህ ውሃ ለማግኘት ሲሉ የሚያደርጉትን የረጅም ርቀት አድካሚ ጉዞ ከማስቀረታቸውም በላይ ማህበረሰቡን ለከፋ የጤና ችግር ሲዳርጉ የነበሩ የውሃ ወለድ በሽታዎችን በዘላቂነት የሚከላከሉ መሆናቸው ተገልጿል።
ከመጠጥ ውሃው በተጓዳኝ የተመረቁት የመስኖ ፕሮጀክቶች ደግሞ በክልሉ የግብርና ሽግግር ለማምጣት ትልቅ ራዕይ የያዙ መሆናቸው ተመላክቷል።
በመስኖ እና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር “የቆላማ አካባቢዎች የኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት” ትብብር የተሰሩ ፕሮጀክቶቹ÷ የክልሉ አርብቶ አደሮች ከቦታ ቦታ መንቀሳቀሳቸውን በመቀነስ ተረጋግተው እንዲኖሩና ከአርብቶ አደርነት ወደ ከፊል አርሶ አደርነት የህይወት ዘይቤ እንዲሸጋገሩ ትልቅ መሰረት የጣሉ መሆናቸውም ተገልጿል።
በምንተስኖት ሙሉጌታ