Fana: At a Speed of Life!

ወሳኙ ጥምረት …

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የግል ዘርፍ በሀገር አካታች ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥ ወሳኝ እና ቀዳሚ ድርሻ አለው።

በኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ዕሳቤ በሆነው “መደመር” መሰረት መንግሥት እና የግል ዘርፍ በአንድ ዓላማ ለሀገራዊ ዕድገትና ብልጽግና በጋራ የሚቆሙ አጋሮች ናቸው።

ከግል ዘርፉ ጋር ያለው ግንኙነት የገበያ ጉድለቶችን በመፍታት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን፤ በሁለንተናዊ ቅንጅትና መደጋገፍ ላይ የተመሰረተ መሆን ይኖርበታል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የቀድሞ መንግሥታት የግል ዘርፉን እንደ ሥጋት ወይም እንደ ተቃራኒ የሚመለከቱበትን የተሳሳተ አመለካከት በመለወጥ መንግሥት ከግል ዘርፉ ጋር ተደጋግፎ የሚሰራበት አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል።

ይህ የአጋርነት መንፈስ በትልልቅ የልማት ሥራዎች ላይ መሰረት የጣለ ሲሆን፤ የንግድ ፈቃድ አሰጣጥን እና አስተዳደራዊ ሒደቶችን ለማቅለልና ለማዘመን የሚያስችሉ ሰፊ ማሻሻያዎች ተደርገዋል።

የፋይናንስ አቅርቦት ላይ በተሰራው ሥራ የባንክ ብድሮች በብዛት ለግል ዘርፉ ተሰጥተዋል።

ከመሰረተ ልማት አንጻርም ለኢንዱስትሪዎች የኤሌክትሪክ ኃይልና የመሥሪያ ቦታዎችን በማመቻቸት፤ በተለይም በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የሚንቀሳቀሱ ዘርፎች ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ተደርጓል።

የፖሊሲና የሕግ ማሻሻያዎች መደረጋቸው የግል ዘርፉ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር አስችለዋል።

ለውጭ ኢንቨስትመንት ብቻ ሳይሆን፤ ለሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ልዩ ትኩረት በመስጠት በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች በመንግሥት የግዥ ሥርዓት ውስጥ ቅድሚያ እንዲያገኙ ተደርጓል።

የፋይናንስ አቅርቦትን በማመቻቸት እና በጥናት ላይ የተመሠረተ ድጋፍ በመስጠት ባለሃብቶች በቴክኖሎጂ የተደገፈና ተወዳዳሪ የሆነ ምርት እንዲያመርቱ መንግሥት አጋርነቱን በተግባር አሳይቷል።

ይህ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አቅጣጫ የሀገር ውስጥ ባለሃብቱ በሀገሩ ሰርቶ እንዲበለጽግና ለኢኮኖሚው ሉዓላዊነት አለኝታ እንዲሆን የሚያስችል ነው።

መንግሥት በቀጣይ ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያን የግል ዘርፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችሉ ጠንካራ የድጋፍ ሥርዓቶችና የትብብር ማዕቀፎች ይዘረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ዋናው ግብ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የንግድ ሥራ ምቹነት መለኪያ መሰረት ቀዳሚ ከሆኑ ሀገራት ተርታ ማሰለፍ ነው።

ይህን ለማሳካት የአሰራር ሥርዓቶችን በቴክኖሎጂ በማዘመን እንዲሁም አድካሚ የቢሮክራሲ ሰንሰለቶችንና ጊዜ ያለፈባቸው ሕጎችን በማሻሻል አመቺ የሆነ ሥነ ምህዳር መፍጠር ያስፈልጋል።

ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ማጠናከር፣ የጋራ ኢንቨስትመንቶችን ማሳደግ እና የመንግሥትና የግል አጋርነት ሥራዎችን ማስፋት ይጠበቃል።

የሀገር ውስጥ ባለሃብቶች አቅማቸውን ገንብተው በዓለም አቀፍ ገበያዎች ላይ በብቃት መወዳደር እንዲችሉ አስፈላጊውን የቴክኖሎጂ ሽግግርና የፋይናንስ አቅርቦት ድጋፍ እንዲያገኙ መሰራት ይኖርበታል።

የግል ዘርፉ በትልልቅ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችና የልማት ሥራዎች ላይ ከመንግሥት ጋር ተቀናጅቶ የሚሳተፍባቸው ማዕቀፎችም በስፋት ይተገበራሉ ተብሎ ይታሰባል።

የግል ዘርፉን የብልጽግና ዋነኛ ሞተር አድርጎ በመውሰድ ኢትዮጵያ ለንግድና ለኢንቨስትመንት ይበልጥ ምቹ፤ በዓለም አቀፍ ባለሃብቶች ዘንድ ተመራጭ እንድትሆን በቁርጠኝነት መስራት ይገባል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.