የዴሞክራሲ ልምምድ የመቅረጽ፣ የመግራት፣ የማስፋት እና የማጽናት ሚና የሚዲያው የቤት ሥራ …
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫን ሀገርን በጽኑ መሠረት ላይ የምንገነባበት እና ስንደመር ምን ያህል ታላቅ ነገር ማድረግ እንደምንችል ለዓለም በተግባር የምናሳይበት የታሪክ አጋጣሚ ማድረግ ይገባል አለ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት።
አገልግሎቱ ባወጣው መረጃ÷ ጀግኖች ከዓደዋ ዜሮ ዜሮ ተነስተው በአንድነት ጸንተው ሀገርን እንዳስረከቡን የሚዲያው ዘርፍም ለኢትዮጵያ ከፍታ በቃል ኪዳን አስሮ ከዚሁ ሥፍራ ስለሀገር በአንድነት ተነስቷል ብሏል።
የዴሞክራሲ ግንባታ የሀገረ መንግሥት ማጽኛ አንዱ ምሰሶ መሆኑ በተመከረበት በዚህ መድረክ፤ የዴሞክራሲ ልምምድ የመቅረጽ፣ የመግራት፣ የማስፋት እና የማጽናት ሚና የሚዲያው የቤት ሥራ መሆኑ በሚዲያ ቤተሰቡ ተሞክሮበታልም ነው ያለው።
በመድረኩ ከ25 በላይ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች በአንድነት መምከራቸውን ገልጿል።
ሚዲያዎች በሀገር ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ እንዴት በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ሰፊ ውይይት በማድረግ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማሳካት የግብዓት እና የሰው ኃይልን በማቀናጀት በጋራ ለመስራት ውል አስረውበታል ሲልም አመልክቷል።