Fana: At a Speed of Life!

ፓርኩ ለጎንደርና አካባቢው የኢኮኖሚ የስበት ማዕከል ሆኖ ያገለግላል – አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የጎንደር የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለአካባቢው የኢኮኖሚ የስበት ማዕከል ሆኖ ያገለግላል አሉ፡፡

ርዕስ መስተዳድሩ ከኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን የጎንደር የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክን ግንባታ አስጀምረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ በክልሉ የግብርናና ኢንዱስትሪ ሽግግርን ለማምጣት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

በአማራ ክልል በቀጣይ አምስት ዓመታት ስምንት የኢኮኖሚ ዞኖች ለማልማት መታቀዱን ጠቁመው፥ የሚያለማውን ባለሀብት መለየትና የልማት መሰረተ ልማቶችን ማሟላት ትኩረት የተሰጣቸው ተግባራት ናቸው ብለዋል፡፡

የአርሶ አደሩን ግብርና ምርትን ጥራት በማሳደግ ለኢንዱስትሪ ፓርኮች መመገብ ከቻለ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዋስትና ማረጋገጥ ይችላል ነው ያሉት።

ግንባታው በፍጥነትና በጥራት መጠናቀቅ አለበት ያሉት ርዕስ መስተዳድሩ፥ ለዚህም የአካባቢው መስተዳድርና የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል።

በክልሉ የአምራች ኢንዱስትሪውን አቅም ለማሳደግ ፓርኮች በስፋት እየተገነቡ ሲሆን፥ ፓርኩ ለአካባቢው የኢኮኖሚ መነቃቃት ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ነው የተገለጸው፡፡

የኢንዱስትሪ ሚንስትሩ መላኩ አለበል በበኩላቸው፥ በሀገር አቀፍ ደረጃ 17 የኢንዱስትሪ ዞኖች መለያታቸውን ገልጸው፥ ከእነዚህም ውስጥ ሦስቱ ግንባታቸው ተጠናቋል ነው ያሉት።

የግብርና ምርቶችን እሴት በመጨመር ፓርኮች ወሳኝ ሚና እንዳላቸው የገለጹት ሚኒስትሩ፥ ባለሀብቶችን ወደ ስራ በማስገባት ውጤታማ ስራ ማከናወን እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኩ በ8 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ወጪ የሚገነባ ሲሆን፥ ለፓርኩ ስራ ከአካባቢው ለተነሱ አርሶ አደሮች 718 ሚሊየን ብር በላይ ካሳ ተከፍሏል፡፡

ፓርኩ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ ለ221 ሺህ ወጣቶች የስራ ዕድል እንደሚፈጥርና በዓመት ከ1 ሚሊየን ቶን በላይ የግብርና ምርቶችን የማቀነባበር አቅም እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

በምናለ አየነው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.