Fana: At a Speed of Life!

በሁሉም የዓለም ዋንጫ የተሳተችፈው ብራዚል…

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብራዚል በዓለም ዋንጫ መድረክ ከምስረታው ጀምሮ በእያንዳንዱ ውድድር ላይ በመሳተፍ ቀዳሚዋ እና ብቸኛዋ ሀገር ናት፡፡

የዓለም ሕዝብ በጉጉት የሚጠብቀው ትልቁ የሀገራት ውድድር የዓለም ዋንጫ በፈረንጆቹ 1930 ነው መደረግ የጀመረው፡፡

ብራዚል ከዓለም ዋንጫ ጅማሮ አንስቶ እስካሁን ድረስ በሁሉም የዓለም ዋንጫ የተሳተፈች ሲሆን ÷ የዘንድሮው ተሳትፎዋ ደግሞ ለተከታታይ 23ኛ ጊዜ ነው፡፡

በዚህም ብራዚል በሁሉም የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ በመሳተፍ እና በተከታታይ ለበርካታ ጊዜ በመድረኩ በመገኘት ቀዳሚዋ ሀገር ናት፡፡

በዓለም ዋንጫ ታሪክ ብራዚል አምስት ጊዜ ሻምፒዮን በመሆን ቀዳሚ ብሔራዊ ቡድን ስትሆን ÷ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ዋንጫን ያሳካችው በፈረንጆቹ 1958 ነበር፡፡

በመቀጠልም በፈረንጆቹ 1962 ሻምፒዮን በመሆን በተከታታይ ዋንጫውን አሳክታለች፡፡ ከተጨማሪም በ1970፣ 1994 እና 2002 ሻምፒዮን በመሆን በመድረኩ አምስት ጊዜ ዋንጫውን በማሳካት ቀዳሚ ናት፡፡

ሆኖም ግን የአምስት ጊዜ የመድረኩ አሸናፊዋ ሀገር ብራዚል በፈረንጆቹ 2014 እራሷ ባዘጋጀችው መድረክ በጀርመን የደረሰባት ሽንፈት የሚረሳ አይደለም፡፡

በወቅቱ ብራዚል በእራሷ ድግስ በጀርመን ብሔራዊ ቡድን አስከፊ የ7 ለ 1 ሽንፈት ማስመዝገቧ ይታወሳል፡፡

ብራዚል ኔይማር ጁኒየርን በሩብ ፍጻሜው በከባድ ጉዳት ማጣቷን ተከትሎ ያለ ወሳኝ ተጫዋቿ ነበር የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታውን ያደረገችው፡፡

ብራዚል በ2014ቱ የዓለም ዋንጫ በግማሽ ፍጻሜው በጀርመን ያልጠበቀችው ሽንፈት ማስተናገዷ የሚታወስ ነው፡፡

በስታዲየሙ የታደሙ የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎች በጭንቀት ተውጠው እና በእንባ ታጅበው ተመሳስሎ የተሰራውን ዋንጫ አቅፈው ጨዋታውን መመለከታቸው አይዘነጋም፡፡

በወቅቱ ብሔራዊ ቡድኑን በአምበልነት እየመራ ወደ ሜዳ የገባው ዴቪድ ሉዊዝ በእንባ ታጅቦ ደጋፊዎቻቸውን ይቅርታ ጠይቋል፡፡

የብራዚል ብሔራዊ ቡድን ደጋፊዎችም የብሔራዊ ቡድናቸውን ማልያ መሬት ላይ በመጣል የረጋገጡ ሲሆን÷ ከዚያም አልፈው ማቃጠላቸው አይዘነጋም፡፡

ብራዚል በ2014 ዓለም ዋንጫ በግማሽ ፍጻሜው በጀርመን የደረሰባት አስከፊ ሽንፈት በዓለም ዋንጫ ወድድር ከማይረሱ ክስተቶች መካከል አንዱ ሆኖ በታሪክ ይወሳል፡፡

ለመጨረሻ ጊዜ በፈረንጆቹ 2002 የዓለም ዋንጫን ያሳካችው ብራዚል ለ6ኛ ጊዜ በመድረኩ ሻምፒዮን ለመሆን በ2026ቱ የዓለም ዋንጫ የምታደርገው ጉዞ ይጠበቃል፡፡

በአሰልጣኝ ካርሎ አንቸሎቲ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑ ኔይማር ጁኒየርን በስብስቡ ውስጥ አካትቷል፡፡

ኦፕታ የ2026ቱን የዓለም ዋንጫ ያሳካል በሚል ባስቀመጠው ቅድመ ትንተና መሰረት ብራዚል 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

ብራዚል የ2026 ዓለም ዋንጫ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዋን የፊታችን እሑድ ከሞሮኮ ጋር የምታደርግ ይሆናል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.