Fana: At a Speed of Life!

ፖርቹጋል ከኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ..

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም ዋንጫው የክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሀገር ፖርቹጋል የመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋን ዛሬ ምሽት ታደርጋለች፡፡
ፖርቹጋል ምሽት 2 ሰዓት ላይ ከኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ጋር በሂውስተን ስታዲየም በምታደርገው ጨዋታ የማሸነፍ ቅድመ ግምት ተሰጥቷታል፡፡
የመጨረሻው የዓለም ዋንጫ ተሳትፎውን የሚያደርገው ፖርቹጋላዊ ኮከብ በጨዋታው ልዩነት ፈጣሪ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
በአውሮፓ የተለያዩ ክለቦች ቁልፍ የሆኑትን ብሩኖ ፈርናንዴዝ፣ ቪቲኒሃ፣ ኔቬስ፣ ሜንዴዝ እና ሊያዮን የመሳሰሉ ኮከቦችን የያዘችው ፖርቹጋል በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን ከፍ የማድረግ አቅም እንዳላትም በርካቶች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡
ተጫዋቾቹ ንጉሳቸውን ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በድል ለመሸኘት የሚያደርጉት ጥረት መነሳሻ እንደሚሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡
ትናንት ምሽት አርጀንቲና ሰሜን አፍሪካዊቷን ሀገር አልጄሪያን ባሸነፈችበት ጨዋታ ሊዮኔል ሜሲ ሀትሪክ መስራቱን ተከትሎ ክሪስቲያኖ ለቡድኑ የሚኖረውን አበርክቶ ለማየት ብዙዎች ጓግተዋል፡፡
የሁለቱ ተጫዋቾች ንጽጽር አሁንም የቀጠለ ሲሆን፥ የምሽቱ የሜሲ አሰደናቂ እንቅስቃሴ ተከትሎ ሮናልዶ ይህን ማድረግ ይችል እንደሆን በርካቶች እየተነጋገሩበት ይገኛሉ፡፡
በሌላ የዛሬ ምሽት መርሐ ግብር እንግሊዝ ከክሮሽያ የምታደርገው ጨዋታ 5 ሰዓት ላይ በዳላሰ ስታዲየም ይከናወናል፡፡
ዴክላን ራይስ፣ ሃሪ ኬን፣ ቡካዮ ሳካ፣ ጁድ ቤሊንግሃምና አንደርሰንን የመሳሰሉ ድንቅ ኮከቦችን የያዘችው እንግሊዝ ለውድድሩ አሸናፊነት ቅድመ ግምት ካገኙ ሀገራት መካከል አንዷ ናት፡፡
በእነ ሉካ ሞድሪች፣ ፐርሲች፣ ኮቫቺች እና ሌሎች አንጋፋ ተጫዋቾች እየተመራች ውድድሯን የምታከናውነው ክሮሽያ ብዙም ግምት ባይሰጣትም ክስተት የመሆን አቅም እንዳላት በተለያዩ ጊዜያት አስመስክራለች፡፡
እንግሊዝ በጀርመናዊው አሰልጣኝ ቶማስ ቱኸል እየተመራች ያሰበችውን ለማሳካት የመጀመሪያ ፈተናዋን ዛሬ ምሽት አንድ ብላ ትጀምራለች፡፡
በአቤል ነዋይ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.