Fana: At a Speed of Life!

የአሜሪካ እና ኢራን የሰላም ውይይት ዛሬ በስዊዘርላንድ ይደረጋል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የ60 ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ የደረሱት አሜሪካ እና ኢራን የመጀመሪያ ዙር ድርድር ዛሬ በስዊዘርላንድ ያደርጋሉ፡፡

ሁለቱ ወገኖች ቀደም ሲል በፓኪስታን አደራዳሪነት ጊዜያዊ ስምምነት ላይ የደረሱ ሲሆን፥ ስምምነቱን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የኢራኑ ፕሬዚዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን መፈረማቸው ይታወሳል፡፡

ዛሬ በስዊዘርላንድ የሚጀምረው የሁለቱ ሀገራት ድርድር ጊዜያዊ ስምምነቱን መነሻ በማድረግ ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቆም የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል፡፡

የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ እና የኢራን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ መሀመድ ቃሊባፍ እንዲሁም ተደራዳሪ ልዑካኖቻቸው በሰላም ውይይቱ ላይ ለመሳተፍ ስዊዘርላንድ መግባታቸው ተዘግቧል፡፡

ከሰላም ውይይቱ አስቀድሞ ኢራን የእስራኤል ጦር በሊባኖስ ላይ እየፈጸመ ያለው ጥቃት ከዋሽንግተን ጋር የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት የሚጥስ ነው በማለት በትናንትናው ዕለት የሆርሙዝ ሰርጥን መዝጋቷን ገልጻለች፡፡

ይህም አሜሪካ እና ኢራን ዘላቂ ስምምነት ላይ ለመድረስ በሚያደርጉት የሰላም ውይይት ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው የተገለጸ ሲሆን፥ የአሜሪካ ጦር በበኩሉ በሰርጡ የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ መቀጠሉን አስታውቋል፡፡

የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ ከሰላም ውይይቱ አስቀድሞ በሰጡት አስተያየት፥ በተለይም በኒውክሌርና በሊባኖስ የተኩስ አቁም ጉዳይ ውጤት የሚገኝበት ድርድር እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሚኒ ከፍተኛ አማካሪ ሞሃመድ ሞክበር በበኩላቸው፥ አሜሪካ በሁሉም ግንባሮች የተኩስ አቁም እንዲደረግ የሚጠይቀውን ባለ 14 ነጥብ የሰላም ስምምነት ተግባራዊ አላደረገችም ሲሉ ወንጅለዋል፡፡

ስምምነቱ ከወረቀት ባለፈ መሬት ላይ የማይወርድ ከሆነ በቀጣናው የነዳጅ እንቅስቃሴ ተቋርጦ ይቆያል በማለት ማስጠንቀቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.