በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ነዋሪዎቻችንን በታማኝነት የማገልገል አቋማችን ፅኑ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ነዋሪዎቻችንን በታማኝነት የማገልገል አቋማችን ፅኑ ነው አሉ፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ከሁለት ወር በፊት የተጀመረው የቅጠል ተራ የቤቶች ግንባታ ሒደት በዛሬው ዕለት መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡
በፕሮጀክቶቹ መኖሪያ ቤቶች ብቻ ሳይሆኑ የንግድ፣ የጸጥታ እና የጤና ተቋማት እንዲሁም ትምህርት ቤት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ፣ የህፃናት መጫወቻን ጨምሮ ማህበራዊ አገልግሎት መስጫዎችና የህዝብ የጋራ መገልገያዎች እንደሚገነቡ ጠቁመዋል፡፡
ከሁለት ወር በፊት የተጀመሩ ህንጻዎች 9ኛ ወለል ላይ የደረሱ ሲሆን፥ ቦታውን ከማጽዳት ጋር በተያያዘ ከአንድ ወር በፊት የተጀመሩ ህንጻዎችም 4ኛ እና 5ኛ ወለል ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡
ከሁለት ሳምንት በፊት የግንባታውን ሂደት ተመልክተን የጨመርናቸው ሶስት ህንጻዎችም ጅማሮ በጥሩ ሂደት ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
የምንገነባው መኖሪያ ቤት ብቻ ሳይሆን ህጻናት ቦርቀው የሚያድጉበት፣ ወጣቶች የአካልና የአዕምሮ ብቃታቸውን የሚያዳብሩበት እንዲሁም ዜጎቻችን አገልግሎቶችን በቅርበት የሚገኙበት ክብራችንን የሚያስጠብቅ ምቹና ፅዱ አካባቢን ነው ብለዋል።
የቅጠል ተራ መኖሪያ መንደርን ትናንት ከተጀመረው የገዳም ሰፈርና የጣሊያን ሰፈር በአንድ ላይ በማልማት የዘመነ አኗኗርና ሰፊ የስራ እድል የሚፈጥር አካባቢ ለማድረግ እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡
በምርጫ ወቅት ላይ ሆነን የፕሮጀክቶቹ ግንባታ ሳይቀዛቀዝ መቀጠሉ በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ነዋሪዎቻችንን በታማኝነት የማገልገል አቋማችን ፅኑ መሆኑን ያሳያል ነው ያሉት።
ህንጻዎቹን በጥራትና በፍጥነት ተገንብተው በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ እየሰሩ ለሚገኙ አመራሮች፣ ሰራተኞችን ጨምሮ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡