አሜሪካ በባንክ ታግዶ የቆየ 12 ቢሊየን ዶላር ለኢራን ለመልቀቅ ተስማማች
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ በማዕቀብ ምክንያት በባንክ ታግዶ የቆየውን 12 ቢሊየን ዶላር ፈንድ ለኢራን ለመልቀቅ ተስማምታለች፡፡
ኢራን በአሜሪካ ማዕቀብ ምክንያት በቻይና፣ ኢራቅ፣ ሕንድ እና ኳታርን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት ከ100 እስከ 120 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ እንዳይንቀሳቀስ ታግዶባት ቆይቷል፡፡
አሜሪካ እና ኢራን ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ በስዊዘርላንድ ያደረጉት ውይይት መጠናቀቁን ተከትሎ ለኢራን መልሶ ግንባታ የሚውል ፈንድ እንዲለቀቅ መወሰኑን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባኤ እና ከፍተኛ ተደራዳሪ መሐመድ ባጋር ጋሊባፍ እንዳሉት÷ በተደረገው ውይይት አሜሪካ በኢራን ነዳጅ ዘይት እና ፔትሮኬሚካል ሽያጭ ላይ ጥላው የነበረውን ማዕቀብ ለማንሳት ተስማምታለች።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ታግዶ የቆየው የኢራን የባንክ ሂሳብ የአሜሪካ የግብርና ምርቶችን ለመግዛት ጥቅም ላይ እንደሚውል ተናግረዋል።
በምላሹ ኢራን በስዊዘርላንዱ ውይይት ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጅ ኤጀንሲ በኢራን የኑክሌር ጣቢያዎች ላይ ቁጥጥር እንዲያደርግ ፈቃዷን ሰጥታለች ተብሏል።
አሜሪካ እና ኢራን ዘላቂ የተኩስ አቁም ለማድረግ ከስምምነት ላይ የደረሱ ቢሆንም እስራኤል በሊባኖስ እያደረገች ያለው ዘመቻ ግን በስምምነቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
እስራኤል እና ሂዝቦላህ ከቀናት በፊት የተኩስ አቁም ስምምነት ቢያደርጉም ሂዝቦላህ የፈጸመውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ እስራኤል መጠነ ሰፊ አፀፋ ሰጥታለች፡፡
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ እስራኤል ደቡባዊ ሊባኖስን ተቆጣጥራ ትቆያለች፤ ሂዝቦላህንም ታጠፋለች ማለታቸው አሜሪካ እና ኢራን በሁሉም የድርድር ሀሳቦች ላይ እንዳይስማሙ እንዳያደርግ ተሰግቷል፡፡
በሚኪያስ አየለ