Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባን በወንዞቿ እንደ ስሟ …

የከተማ ወንዞች የአንድ ከተማ የሕይወት መስመር፣ የተፈጥሮ ሳንባ እና የውበት መገለጫዎች ናቸው።
በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ከተሞች የተመሠረቱትና ያደጉት በወንዞች ተፋሰሶች ላይ ቢሆንም፣ በሕዝብ ቁጥር መጨመርና በኢንዱስትሪ መስፋፋት ምክንያት ጥበቃ ስለማይደረግላቸው ከፍተኛ የብክለት ጫና ያርፍባቸዋል።
ወንዞች በተፈጥሯዊ ሁኔታቸው ንፁህ እና ሕይወት ያላቸው ናቸው፡፡ የተበከሉ የከተማ ወንዞች ደግሞ የአንድን ከተማ ሥነ-ምህዳር የሚያበላሹ፣ የነዋሪዎችን ጤና አደጋ ላይ የሚጥሉ እና የከተማዋን ገጽታ የሚያጠፉ ይሆናሉ፡፡
ወንዞች የከተማ ሳንባዎች እንደመሆናቸው እነሱን ማጽዳት የአካባቢ ጥበቃ፣ የጤና እና የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ ይረዳል፡፡
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ሸገርን በማስዋብ ፕሮጀክት ትኩረት ከሰጠቻቸው መስኮች መሀከል አንድ የወንዞች ዳርቻ ልማት ነው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በአጠቃላይ የ56 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት በተለያዩ ምዕራፎች ተከፋፍሎ እየተተገበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት እስከ 49 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የልማት ሥራ በስምንት ወንዞች ላይ እየተከናወነ ይገኛል።
1. ከእንጦጦ – ቀጨኔ መድኃኔዓለም፡-
ከእንጦጦ እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም ያለው መስመር በቅርቡ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ተመርቆ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት ተደርጓል፡፡ ይህ የወንዝ ዳርቻ ልማት 22.25 ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡ ፕሮጀክቱ የአፈር መሸርሸር መከላከያዎችን፣ የፍራፍሬ መናፈሻዎችን፣ የብስክሌትና የእግረኛ መሄጃ መንገዶችን እንዲሁም ዘመናዊ የውሃ ማጣሪያ ሥርዓቶችን ያካተተ ነው።
2. የእንጦጦ – ፒኮክ መስመር፡-
የውስጥ መንገዶችን ሳይጨምር 21 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን፣ በከተማዋ ትልቁን ድርሻ የያዘ የመጀመሪያው ምዕራፍ የወንዝ ዳርቻ ልማት የስኬት ማሳያ ነው።
3. የቀበና እና ግንፍሌ ወንዞች መስመር፡-
በአጠቃላይ 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የልማት ኮሪደር ሲሆን የአካባቢውን ሥነ-ምህዳር ለመጠበቅና ለነዋሪዎች ምቹ ለማድረግ ተገንብቷል።
4. የቁርጡሚ ወንዝ፡-
ይህ የወንዝ ዳርቻ ልማት 2.2 ኪሎ ሜትር የሚረዝም ሲሆን የከተማዋ አዲስ የቱሪስትና የመዝናኛ ማዕከል ሆኖ ለምቷል።
ሰባት ሄክታር አረንጓዴ ስፍራ፣ አምስት አምፊቲያትሮች (የኪነ-ጥበብ መድረኮች)፣ የልጆች መጫወቻ እና እስከ 500 መኪናዎችን መያዝ የሚችል ባለ 3 ወለል የመሬት ውስጥ መኪና ማቆሚያ (የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ መሙያ ያለው) ተካቶበታል።
በአጠቃላይ በወንዞች ዳርቻ ልማት ከወንዞቹ ግራና ቀኝ ከ30 እስከ 50 ሜትር የሚደርሱ የወንዝ ዳርቻ ቦታዎች ወደ አረንጓዴ ኮሪደርነት ተቀይረዋል።
የእግረኛና የብስክሌት መጋለቢያ መንገዶች፣ የሕዝብ መሰብሰቢያ አደባባዮች፣ ሰው ሠራሽ ፏፏቴዎች እና ለንግድ የሚሆኑ መናፈሻዎች ተገንብተዋል።
ቀደም ሲል ለቆሻሻ መጣያነት ያገለግሉ የነበሩ ቦታዎችን ወደ ፅዱ አየር እና ከጎርፍ አደጋ የተጠበቁ ለማድረግ የወንዝ ማጣሪያና የእርከን ሥራዎችም ተከናውነዋል።
ይህ የወንዞች ዳርቻ ልማት በአጭር አመታት እየተሳካ ያለ ቢሆንም፣ መዲናዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ለቱሪዝም ሳቢ ለማድረግ የተጀመረ የረጅም ጊዜ የኢንቨስትመንት አካል ነው፡፡
በፕሮጀክቶቹ በሺህ ለሚቆጠሩ ወጣቶች በአረንጓዴ ጥበቃ፣ በካፌዎችና በንግድ ቦታዎች ላይ ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።
ይህ ሥራ አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ምቹ ከማድረጉም በላይ ዓለም አቀፍ የቱሪስት መዳረሻነቷንም ከፍ አድርጓል
አዲስ አበባ በዚህ ረገድ በሠራቻቸው የልማት ሥራዎች የ‘ብሪዝ ሲቲስ’ (Breathe Cities) አባል ሆና ተመርጣለች፡፡
አዲስ አበባ የ’ብሪዝ ሲቲስ’ ፕሮግራምን መቀላቀሏ በከተማዋ የአየር ጥራትን ለማሻሻል የሚከናወነውን ሥራ ይበልጥ ያጠናክረዋል።
የ’ብሪዝ ሲቲስ’ ፕሮግራም አሁን ከተቀላቀሉት አዲስ አበባ እና ማድሪድ በተጨማሪ አክራ፣ ባንኮክ፣ ቦጎታ፣ ብራስልስ፣ ጃካርታ፣ ጆሃንስበርግ፣ ለንደን፣ ሜክሲኮ ሲቲ፣ ሚላን፣ ናይሮቢ፣ ፓሪስ፣ ሪዮ ዲ ጄኔሮ፣ ሶፊያ፣ እና ዋርሶ ከተሞች ይገኙበታል።
ኑ፤ ሀገር እንሥራ!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.