Fana: At a Speed of Life!

ባለስልጣኑ አዳዲስ የሕንጻ ኮዶችና ስታንዳርዶችን ሥራ አስጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን የዘርፉን አሰራር የሚያዘምኑ አዳዲስ የሕንጻ ኮዶችና ስታንዳርዶችን መተግበር ጀምሯል፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ዴዔታ የትምጌታ አስራት (ዶ/ር) በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት÷ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡
መንገዶች፣ ድልድዮች፣ ፋብሪካዎች፣ ሆስፒታሎች፣ ት/ቤቶች እና ሌሎች መሰረተ ልማቶች የሀገሪቱን ልማት የሚያንቀሳቅሱ ዋና ሞተሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የግንባታ ሥራዎች በጥራት እና ደህንነት ካልተደገፉ ለሰው ሕይወት መጥፋት እንዲሁም የሃብት ብክነት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አመልክተዋል፡፡
በመሆኑም የግንባታ ደህንነት በሳይንስ፣ በምህንድስና፣ በሕግ እና በስታንዳርድ ሥርዓቶች ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት፡፡
በዘርፉ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የሕግና የቁጥጥር ሥርዓቶችን ማዘመን፣ የቢዝነስ ከባቢን ማሻሻል፣ የባለሙያዎች ብቃት ማረጋገጫን ማጠናከርና የዲጂታል አሰራር ሥርዓቶችን ማስፋፋት ላይ ትኩረት መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ዘርፉ ትራንስፎርሜሽን ከጥራት ቁጥጥር ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የዲጂታል አሰራር፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ ሕንጻዎች መገንባትን እንደሚያካትት አስረድተዋል፡፡
በዚህ ሒደት ውስጥ የብሔራዊ የሕንጻ ኮዶችና ስታንዳርዶች ትግበራ ዋና ለዘርፉ ምሰሶ መሆኑን ሚኒስትር ዴዔታው አረጋግጠዋል።
በግዛቸው ግርማዬ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.