ኢትዮጵያና ቡሩንዲ ለአፍሪካ ሰላምና ብልጽግና በጋራ ለመሥራት የተሳሰሩ ናቸው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ቡሩንዲ ለአፍሪካ ሰላም እና ብልጽግና በጋራ ለመሥራት የተሳሰሩ ናቸው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
የቡሩንዲ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ኢቫሪስት ንዲያሺሚዬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) እና ብልጽግና ፓርቲ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በማሸነፋቸው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ይህን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ እንዳሉት÷ ፕሬዚዳንት ኢቫሪስት ንዲያሺሚዬ በራሳቸው፣ በሀገራቸውና በአፍሪካ ሕብረት ስም ያስተላለፉት የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ለኢትዮጵያ ትልቅ ብርታት ነው።
ሁለቱ ሀገራት በወንድማማችነት እንዲሁም ለአፍሪካ ሰላም እና ብልጽግና በትብብር ለመሥራት በጋራ ቁርጠኝነት የተሳሰሩ መሆናቸውን አውስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለዚህ የሁለትዮሽ ወዳጅነት የላቀ እና ትልቅ ዋጋ እንደምትሰጥ ጠቅሰው ÷ በቀጣይም የሀገራቱን ሕዝቦች ዘላቂ ጥቅም ለማስጠበቅ ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል፡፡