በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሃሰን ክልላዊ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትን በዛሬው ዕለት በአሶሳ ከተማ በይፋ አስጀምረዋል።
አቶ አሻድሊ በዚህ ወቅት÷ በለውጡ መንግሥት የዜጎችን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የተለያዩ ሀገራዊና ክልላዊ ኢኒሼቲቮች እየተተገበሩ ነው ብለዋል፡፡
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የአብሮነትና መረዳዳት ባሕልን በማጠናከር የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በክልሉ ከ2 ሺህ 300 በላይ የአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታ እና እድሳት ሥራ መከናወኑን ነው ያስረዱት፡፡
በተያዘው ክረምት ከ100 በላይ የአቅመ ደከማ ቤቶች ግንባታና ዕድሳት ሥራ ፣ የአረንጓዴ ዐሻራ፣ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ የማዕድ ማጋራትን ጨምሮ የተለያዩ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስረድተዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ ሕዝብ በመርሐ ግብሩ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ ማቅረባቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።