Fana: At a Speed of Life!

የዓለም ዋንጫ የምድብ 3ኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይደረጋሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም ዋንጫ የምድብ 3ኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይደረጋሉ፡፡

ምሽት 5 ሰዓት ላይ አስቀድማ ማለፏን ያረጋገጠችው ጀርመን ከኢኳዶር ጋር ጨዋታዋን የምታደርግ ይሆናል፡፡

ሁለቱንም የምድብ ጨዋታዎች ድል ያደረገችው ጀርመን በስድስት ነጥብ ምድቡን እየመራች ትገኛለች፡፡

ተጋጣሚዋ ኢኳዶር በበኩሏ ካደረገቻቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ በመያዝ በምድቡ 3ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

በዚሁ ምድብ በተመሳሳይ ሰዓት ኩራሳኦ ከኮትዲቫር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

ኮትዲቫር ሦስት ነጥብ በመሰብሰብ በምድቡ 2ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠች ሲሆን÷ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ መድረክ የተገኘችው ኩራሳኦ በአንድ ነጥብ የምድቡ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

በሌላ ጨዋታ መሰናበቷን አስቀድማ ያወቀችው ቱኒዚያ ሌሊት 8 ሰዓት ላይ ከኔዘላንድስ ትጫወታለች፡፡

ኔዘርላንድስ አራት ነጥብ በመሰብሰብ ምድቡን ስትመራው አፍሪካዊቷ ሀገር ቱኒዚያ ያለምንም ነጥብ ከመድረኩ ላለመሰናበት በጨዋታው የምታደርገው ፉክክር ይጠበቃል፡፡

በዚሁ ምድብ በተመሳሳይ ሰዓት ጃፓን ከስዊድን የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡

ጃፓን በአራት ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጣ 2ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ተጋጣሚዋ ስዊድን ደግሞ በሦስት ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.