Fana: At a Speed of Life!

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባሕላዊ ፍርድ ቤቶችን ለማጠናከር እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህል ዳኝነት በማሕበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን በመፍታት ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው አለ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፡፡

በቢሮው የባሕል ዘርፍ ኃላፊና የቢሮ ም/ኃላፊ ደግነህ ቦጋለ እንዳሉት÷ ባሕላዊ ዳኝነት በማሕበረሰቡ ውስጥ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንና ግጭቶችን በመፍታት ረግድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡

በዚህ መሰረትም የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከክልል እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የባሕል ሽማግሌዎች ፎረምን በማጠናከር በሰላም ግንባታ ሥራ ላይ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ነው ብለዋል፡፡

ፎረሙን የማጠናከር እና የሀገር በቀል እውቀቶችን የመሰነድ ሥራ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ ደግነህ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል።

ክልሉ የበርካታ ሀገር በቀል እውቀቶችና የባህል እሴቶች ጸጋ ባለቤት መሆኑን ጠቅሰው÷ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የባህል ሀገር ሽማግሌዎች ፎረም ተደራጅቶ በርካታ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

አለመግባባቶችና ግጭቶች ሲከሰቱ በባሕላዊ መንገድ በመፍታት ክልሉ ሰላም መለያ እሴቱ እንዲሆን በቁርጠኝነት እየተሰራ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

በቅርቡ የባህል ፍ/ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ጸድቆ ተግባራዊ እየተደረ መሆኑን ያስረዱት አቶ ደግነህ ÷ ከባለድርሻ አካላት ጋር በተደረገ ቅንጅታዊ ሥራ ወንጀሎች በእጅጉ መቀነሳቸውንና የማሕበረሰቡ እርስ በርስ ትስስር መጠናከሩን ገልጸዋል ።

የባህል ዳኝነት ማሕበረሰቡ ለዘመናት ጠብቆ ያቆየው የሀገር በቀል እውቀት ነው ፤ ይህንን ሀብት ትርጉም ባለው መልኩ ጥቅም ላይ ለማዋል ለባህል ሽማግሌዎች ፎረም ተከታታይ ስልጠና በመስጠት መጠናከሩን ተናግረዋል።

ባህላዊ ዳኝነቱ ከዘመናዊ ፍ/ቤቶች በተለየ ግጭቶችን በግልግል እና በዕርቅ በመፍታት የተበዳዩን እና በዳዩን ቀጥተኛ ግንኙነት የሚጠግን አደረጃጀት እንደሆነ አስገንዝበዋል።

በሀገራዊ ምክክር ጉባዔ አጀንዳዎች መሳካት ውስጥ የሀገር ሽማግሌዎች ፎረም ሚና ከፍተኛ እንደነበር ጠቁመው ÷ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር፣ በማሕበረሰቡ መካከል ቅራኔ፣ ቁርና ኩርፊያ እንዳይኖር የሀገር ሽማግሌዎች መስራት አለባቸው ነው ያሉት።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የባሕል ሽማግሌዎች አደረጃጀት ማጠናከሪያና የባህል ዳኝነት ጽንሰ ዓሳብ ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና በሆሳዕና ከተማ እየተሰጠ ይገኛል።

በተካልኝ ሃይሉ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.