ቁጠባን መሰረት ያደረገ የበጀት አጠቃቀም አስፈላጊ ነው – አቶ አሕመድ ሽዴ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ቁጠባን መሰረት ያደረገ የበጀት አጠቃቀም አስፈላጊ ነው አሉ የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ፡፡
በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ረቂቅ በጀት ላይ ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከባለበጀት መስሪያ ቤቶች ጋር የማጠቃለያ ውይይት አካሂዷል።
አቶ አሕመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ቁጠባን መሰረት ያደረገ የበጀት አጠቃቀም አስፈላጊ ነው፡፡
ከአሁን በፊት የተጀመሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ብቻ እስከ 2 ትሪሊየን ብር እንደሚያስፈልግ ገልጸው÷ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚያስፈልጉትን በመለየት ደረጃ በደረጃ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ አብራርተዋል፡፡
ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጀት ጋር በተያያዘ በቀጣይ በጥናት እንደሚመለስም ነው ያስረዱት፡፡
ጥናቱ ሲጠናቀቅ በተለይም የዩኒቨርሲቲ ጤና ፕሮጀክቶች ወጪ ላይ የክልል መንግሥታትም የራሳቸውን ኃላፊነት የሚወስዱበት አሰራር ሊኖር እንደሚችል አመልክተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ በበኩላቸው÷ የበጀት ዓመቱ የበጀት አመዳደብ ዕቅድ የራስን ወጪ በራስ አቅም ለመሸፈን ታልሞ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
80 በመቶውን በጀት ከሀገሪቱ ገቢ ለመሰብሰብ የታሰበ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን 10 ዓመት መሪ ዕቅድ እና ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ለውጥ መሰረት ያደረገ የበጀት ድልድል እንደሆነ ጠቁመዋል።
ከ4 በመቶው በላይ የነበረውን የሀገር ውስጥና የውጭ ዕዳ መጠን ወደ 1 ነጥብ 4 በመቶ ዝቅ ማድረግ እንደተቻለ እና 30 በመቶ የተያዘው በጀትም ይህንን ዕዳ ለመክፈል የሚውል እንደሆነ አብራርተዋል።
በበጀት ዓመቱ አስፈላጊ የሆኑት ትምህርት፣ ጤና፣ ግብርና፣ መንገድ እና የከተማ ልማት ከፍተኛው በጀት ከተያዘላቸው ዘርፎች እንደሆኑ ጠቁመዋል።
ለመጪው ትውልድ ከዕዳ ነፃ ሀገር ለማስረከብ መንግሥት ከተያዘው በጀት ውስጥ 500 ቢሊየን ብሩን ለዕዳ ክፍያ ጫናን ለመቀነስ የተያዘው በጀት አበረታች እንደሆነ መጥቀሳቸውንም የም/ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡