ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በግንቦትና ሰኔ ወራት በተለያዩ ዘርፎች ያከናወኗቸው ተግባራት፡-
በግንቦት እና ሰኔ 2018 ዓ.ም ወራት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ፣ በቱሪዝም፣ በአረንጓዴ ዐሻራ፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ፣ በሀገር በቀል ሪፎርም እና ቀጣናዊ ዲፕሎማሲ ዙሪያ ላይ ያተኮሩ የተለያዩ ከፍተኛ የሥራ ክንውኖችን አድርገዋል።
- ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ
ግንቦት 23 ቀን 2018 ዓ.ም. በተካሄደው 7ኛው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትውልድ ስፍራቸው በሻሻ ወረዳ በመገኘት ድምጻቸውን የሰጡ ሲሆን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክትም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እና ለሀገር ፍቅር ላሳየው ቁርጠኝነትና ለከፈለው መስዋዕትነት ታላቅ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ይህንኑ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በሰኔ 14 ቀን 2018 ዓ.ም የምርጫ ውጤቱን በይፋ ያወጀ ሲሆን በተመዘገበው ስኬት የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲሁም የሀገራት መሪዎች የደስታ መግለጫና የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክቶችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አድርሰዋል።
- አረንጓዴ ዐሻራ
የ2018ዓ.ም አረንጓዴ ዐሻራ መርሃ-ግብር ማስጀመሪያ በሰኔ ወር የተከናወነ ሲሆን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚሁ ኩነት ላይ ተገኝተው ዐሻራቸውን በማሳረፍ የዚህን ዓመት ሀገር አቅፍ ንቅናቄ በይፋ አስጀምረዋል። በዚህ ዓመት 8 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል የታቀደ ሲሆን መርሃ-ግብሩ ቀደም ሲል ከታለመለት 48 ቢሊዮን ችግኞች ግብ ወደ 65 ቢሊዮን ችግኞች ከፍ ብሏል።
ለዚህም ትልም መሳካት ‘’ተስፋን እንትከል’’ በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ሀገር አቀፍ ኩነቶች ላይ ዜጎችና መሪዎች በጽናት ዐሻራቸውን በማሳረፍ ላይ ይገኛሉ። የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ለአየር ንብረት ጥበቃ ከሚያበረክተው መሠረታዊ አስተዋፅዖ ባለፈ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የማር ምርት ላይ ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ የሚገኝ ሲሆን፤ ተፈጥሮንና አካባቢን በመጠበቅ የደኖች መስፋፋት ተፈጥሯል ይህም የንብ ማንባትን የሚያግዙና የማር ምርትን የሚያሳድጉ ምቹ ከባቢዎችን በመፍጥር የስርዓተ ምግብ መሻሻልን አረጋግጠዋል።
- ዲጂታል ኢትዮጵያ
የዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞን እውን ለማድረግና ለማፋጠን ተተኪውን ትውልድ ማብቃትን ታሳቢ አድርጎ በሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም የተጀመረው የ«5 ሚሊየን የኢትዮጵያ ኮደሮች» መርሐ-ግብር ታቅዶለት ከነበረው የሦስት ዓመታት ጊዜ ቀድሞ ከሁለት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ መሳካቱን በማስመልከት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ህዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
በስልጠናው 5,005,146 ሰልጣኞች የተመዘገቡ ሲሆን ከ3 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ስልጠናውን አጠናቀዋል፤ እስከ ነሐሴ 2018 ዓ.ም ድረስም የሰልጣኞችን ቁጥር 7 ሚሊዮን ለማድረስ የታቀደ ሲሆን ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለውም ወጣት ተማሪዎች መጪውን ክረምት ይህን ታላቅ ዕድል በመጠቀም ክህሎታቸውን እንዲያሳድጉና ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው የዲጂታል መሪ እንዲሆኑ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፤ በተመሳሳይም «ዲጂታል ለልህቅት» በሚል ስያሜ የተዘጋጀ ጉባኤ ላይ የተሳተፉት ጠቅላይ ሚንስትሩ በተለያዩ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በአንድ መድረክ የሚያጣምረውን በአፍሪካ ተቀዳሚ የሆነውን የ’መሶብ’ የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያ በይፋ መርቀዋል። ይህ አገልግሎት የኢትዮጵያ ትልሞች ከተራ ምኞት ባሻገር በዜጎቿ እጆችና አቅም የሚገነባ እውነታ ምስክር ማሳያ ነው ብለዋል።
- የሚኒስትሮች ም/ቤት ስብሰባ
በሰኔ ወር የሚኒስትሮች ምክር ቤት 56ተኛ እና 57ተኛ መደበኛ ስብሰባ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት የተካሄደ ሲሆን በ56ተኛ መደበኛ ስበሰባው ላይ ምክር ቤቱ የመካከለኛ ዘመን (2019-2023) የማክሮ ኢኮኖሚና ፊስካል ማዕቀፍ ላይ እንዲሁም የ2019 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት የበጀት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቶ ቁልፍ ውሳኔዎችን አስተላልፏል፤ በተመሳሳይ በ57ተኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ በፋይናንስ ድጋፍና ብድር ስምምነቶች፣ የአገልግሎት ተቋማት የአገልግሎት ክፍያ ወሰን፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እና የከተማ ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
- ፕሮጀክቶች ጉብኝት እና ምረቃ
በአፍሪካ ታሪክ ግዙፉ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥር 2 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ መጀመሩ ይታወሳል ይህም ሲጠናቀቅ በዓመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የሚያስተናግደውና የቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅምን በ4.4 እጥፍ የሚበልጠው ይህ ፕሮጀክት ሀገራችንን ቀዳሚ የአቪዬሽን ማዕከል ያደርጋታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም በዚሁ ስፍራ ተገኝተው የፕሮጀክቱን አሁናዊ ሁኔታና አመርቂ የእድገት ምዕራፍ ጎብኝተዋል። በተያያዘም ሥነ-ምህዳርንና የከተማ ግብርናን የሚያቀናጀውን ከእንጦጦ እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም የመልሶ ማልማት ፕሮጀክት በይፋ ያስጀመሩ ሲሆን፣ መዲናችንን የቱሪዝም ማዕከል የሚያደርገውን የ87.6 ሄክታር የእንጦጦ-ቀበና የወንዝ ዳርቻ ልማትን መርቀዋል፤ በጥራትና ፍጥነት እየተከናወኑ ያሉ የ3D ህትመትና የኮንቴይነር መኖሪያ ቤቶች ግንባታ አሁናዊ አፈጻጸምንም ተመልክተዋል።
- ዲፕሎማሲ እና የሁለትዮሽ ግንኙነቶች
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከተመራ የአፍሪካ ህብረት የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ጋር የተወያዩ ሲሆን የአፍሪካ ተቋማት በአኅጉሪቱ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ላላቸው ቁልፍ ሚና የላቀ እውቅና ሰጥተዋል። ይህ የአህጉራዊ ተቋማትን አቅም የማጠናከር ተግባር ወደ ቀጠናዊ ትብብርም በመሻገር፣ ከሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ጋር በሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ፣ ደህንነት እና ቀጠናዊ መረጋጋት ዙሪያ ወደ ተደረገ ፍሬያማ ውይይት አምርቷል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ አጋጣሚ የሁለቱ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ከድንበር ባለፈ በጋራ ህዝቦች እና በማይነጣጠል እጣ ፈንታ ላይ የተመሰረተ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውታል።
- ከሰኔ ወር ክንዋኔ ውስጥ በ«ኢትዮጵያ ታከናውናለች» የተሰኘ ጉባዔ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሳተፉ ሲሆን ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ መዋቅር፣ በግብርና፣ በማዕድን፣ በኢንቨስትመንትና መሰል ዓበይት መስኮች ላይ ከለውጥ ባሻገር ወደ ዘላቂ ሽግግር ለመድረስ የወሰደቻቸውን ቆራጥ እርምጃዎችና እምርታዎቻቸው ላይ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፤ ጠቅላይ ሚንስትሩም የተገኙት ለውጦች በአጋጣሚ የተገኙ ድሎች ሳይሆኑ ይልቁንም በመደመር መንፈስ ላይ ተመስረተው በጽናት፣ በጋራ በመቆም በተወሰዱ ቆራጥ እርምጃዎች መሆናቸውን ጠቁመው፣ እነዚህን ድሎች ዘላቂ ለማድረግ የጋራ ትብብርና የትውልድ ቅብብሎሽን የሚሻ መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ጥሪ አስተላልፈዋል።
- የክረምቱን መቃረብ ተከትሎም፣ በጎሮ ወረዳ የ20 አዳዲስ ቤቶች ግንባታን የሚያካትተው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘመቻ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጀምሯል። እነዚህን ግዙፍ መሠረተ-ልማቶች ከሀገራዊ ንቅናቄው ጋር በማስተሳሰር፣ የሚሰራ እጅ፣ የሚናገር አፍ እና የሚያስብ አእምሮ የተናበቡበት ስኬታማ ታሪክ በወሩ ተመዝግቧል።
- የግንቦትና ሰኔ 2018ዓ.ም አጋማሽ ክንዎኖች በቱሪዝም ውይይት የተጠናቀቀ ሲሆን በዚህ ቃለ-መጠይቅ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቱሪዝም ዋነኛ የኢኮኖሚ ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ማንነት ነጸብራቅም መሆኑን ገልጸዋል። የቅርስ አጠባበቅ ላይ የተደረጉ ለውጦችን እና የተፈጥሮ ተስማሚ እንዲሁም የኩነት ቱሪዝም መስፋፋትን አንስተው እነዚህም የጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፤ በዚህም ኢትዮጵያ በዘንድሮው ዓመት 1.4 ሚሊዮን ጎብኚዎችን አስተናግዳ ከ5.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ የቱሪዝም ገቢ አግኝታለች።