በየአካባቢው የሚከወኑ ሥራዎች ኢትዮጵያን ወደምናስበው ከፍታ የመውሰድ አቅም አላቸው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በየአካባቢው እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ኢትዮጵያን ወደምናስበው ከፍታ የመውሰድ አቅም አላቸው አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የገጠር ኮሪደር ልማት አካል የሆነውን ዘመናዊ የሀማሳ ሞዴል መንደር በዛሬው ዕለት መርቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት÷ የተሰራው የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ የአካባቢው አርሶ አደሮች የተሻለ ኑሮ መኖር እንዲችሉ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
አምና በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎቸ በገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ መንግሥት ሞዴል ቤቶችን መስራቱን አስታውዋል፡፡
ዘንድሮ ብዙ ቦታ ላይ ነዋሪዎች ራሳቸው እየሰሩ መሆኑን ጠቅሰው÷ በምዕራብ አባያ የገጠር ኮሪደር ልማት ሥራ ሞዴል ቤቶች የተገነቡት ሙሉ ለሙሉ በአርሶ አደሩ ወጪ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
እኛ ከማሰልጠንና ድጋፍ ከማድረግ ውጪ ሙሉ ለሙሉ ወጪው የተሸፈነው በአካባቢው አርሶ አደር ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
አርሶ አደሩ የአትክልት፣ ፍራፍሬ፣ ማር፣ ዓሳ፣ ዶሮ እና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በጓሮው እያመረተ ተጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ንጽህና እና ምግብ ካለ ጤና አለ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ÷ እነዚህ ጉዳዮች ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በዚህም የዜጎችን ሕይወት መቀየር እንደሚቻል ጠቁመው÷ በትኩረት ከሰራን ኢትዮጵያን ወደምናስበው ከፍታ የመውሰድ አቅም አላቸው ብለዋል፡፡
አርሶ አደሮች በጓሮ ማምረት ከቻሉ ብዙ ጉዳዮች እየቀለሉ እንደሚሄዱ ጠቁመው÷ አርሶ አደሮች የጀመሩትን መልካም ጅማሮ ማጠናከር እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
የተጀመሩት መልካም ሥራዎች እንዲስፋፉ ድጋፍ እናደርጋለን ፤ሥራውን አብረን ማስፋት ይኖርብናል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ