Fana: At a Speed of Life!

ትዝታ እና አዲስ መልክ በቀበና ሲገለጥ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ወንዞች የሰው ልጅ ታሪክ ሕያው ቤተ-መዘክር ናቸው። የሚፈሱት በመሬት በሸለቆዎች እና በደልዳላ መሬት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በዳርቻዎቻቸው በሚኖሩ ሰዎች የጋራ የትዝታ መስክ ጭምር ነው።

በዓለማችን ታላላቅ ከተሞች ወንዞች ሁልጊዜም የስልጣኔ መገኛ፣ የዕለት ተዕለት ኑሮ መደገፊያ እና የመዝናኛ ስፍራዎች ሆነው ቆይተዋል። ወንዞቿ እና ነዋሪዎቿ በትዝታ ገመድ ለተሳሰሩባት አዲስ አበባም የቀበና ወንዝ ለመዲናዋ የትናንት ትዝታ የዛሬ ግስጋሴ እና ቀጣይ ተስፋ ህያው መዳረሻ ነው፡፡

 

አዲስ አበባን ለመረዳት ቀበናን ማወቅ ያለው ፋይዳ ቀላል አይደለም። ለበርካታ ትውልድ ነዋሪዎች፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት ከመካከለኛ እድሜ እና ከዚያ በላይ ለሆኑት ወንዙ የልጅነታቸው እና የወጣትነታቸው ሕያው የምስል አልበም ነው።

ለመዲናይቱ ነዋሪዎች በፀሐያማ ቀኖቻቸው በወንዙ ዳር የደመቁ ከሰዓቶቻቸው፣ በውኃው ላይ ያስተጋባው የልጅነት ሳቃቸው እና የዋና ጊዜ ፈንጠዝያቸው ከዛሬው ምናባቸው ጋር በቀበና ላይ ተሰናስለዋል፡፡

ቀበና ከአዲስ አበባ የከተሜነት ጉዞ ጋር እጅጉን በመተሳሰሩ ስያሜውን ለመዲናይቱ የተለያዩ ክፍሎች አጋርቷል፡፡ ቀበና ሰፈር፣ ቀበና ድልድይ እና ቀበና አቦ የመሳሰሉ ስፍራዎች ከወንዙ የተወለዱ መጠሪያዎች ናቸው፡፡ ይህም ወንዙ ከውኃ አካልነቱ በላይ መሆኑን ያረጋግጣል። በአካባቢው እና ከዚያም ባሻገር ላሉ ነዋሪዎች ወንዙ ከማንነታቸው ጋር ተሳስሯል፡፡

ለዚህም ይመስላል ይህ በመዲናዋ ነዋሪዎች እና በወንዙ መካከል ያለው ጥልቅ ስሜታዊ ትስስር በዕውቁ ድምፃዊ ፀሐዬ ዮሐንስ ቅኔ የተዘረፈለት። የድምጻዊው “ቀበና” የተሰኘው ተወዳጅ ዜማ፣ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ናፍቆት ትዝታን የሚቀሰቅስ ነው።

የፀሐዬ በዜማ የተዋበ ግጥም የቀበናን ተፈጥሯዊ አነሳስ ከጉዞው ጋር አሰናስሎ ያወድሳል፡፡

ደራሽ ውኃ ከላይ

ከእንጦጦ ዲልዲላ

አጎዛን ተሻግሮ

ተባለ ቡልቡላ

ድምጻዊው በሚያምር የቅኔ ለዛ፣ ከእንጦጦ ከፍታዎች የሚወርደውን፣ የከተማይቱን ዝቅተኛ አካባቢዎች እያረሰረስ የሚፈሰውን እንደ መድረሻው ስሙን እየቀያየረ የሚጓዘውን የቀበና ውኃ ጉዞ በዜማ ያስውበዋል፡፡

ሽሮ ሜዳ ነኝ ወንዜ ቀበና

የፈረንሳይ ነኝ ወንዜ ቀበና

ቢሻን ቢሻን ቀበና

እያለ የየአካባቢዎቹን ነዋሪዎች ትዝታ ይተርካል፡፡

ድምጻዊት አለም ከበደም፤

ብርዱ ከቀና ከቀና

ሾላ ቆይተን ቀበና

በማለት ቀበና የህይወት ሙቀት የማይለዬው ስፍራ መሆኑን “አራዳ” በሚለው ዜማዋ ታወሳለች፡፡

ከተሞች ሲያድጉና ሲዘምኑ፣ በውስጣቸው ያሉት የተፈጥሮ መዳረሻዎች በእኩል ካልተጓዙ አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡ ከዘመናዊነት ጋር አብረው እንዲጓዙ አዲስ ውበትን ሊላበሱ ግድ ይላቸዋል።

በተለይም እንደ ወንዞች የመሳሰሉ ተፈጥሯዊ ሃብቶች አስፈላጊነት ዘመን ተሻጋሪ ለማድረግ፣ ዘመናዊ መሰረተ ለማቶች እና ከከተሞች ሥነ-ምህዳር ጋር የተናበበ ልማትን ይሻሉ፡፡

ይህን ታሳቢ ያደረገው እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት እና ቅርብ ክትትል ተጠናክሮ የቀጠለው የአዲስ አበባ የወንዞች ዳርቻ ልማት የአፍሪካ የዲፕሎማሲ እና የባህል ማዕከል የሆነችውን አዲስ አበባን ስሟን የሚመጥን አዲስ መልክ እያላበሳት ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ቀበናን ከትዝታ ማኅደርነት አውጥቶ ወደ ዘመናዊ የከተማ ውብ መዳረሻነት የቀየረ ሰፊና ዘርፈ-ብዙ ፕሮጀክት አከናውኖ ከዳር አድርሷል፡፡ ይህም በአዲስ አበባ እየተከናወነ ባለው የከተማ ገጽታ ሽግግር ጉዞ ላይ ትልቅ ምዕራፍ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ይህ ተነሳሽነት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እና የከተማ ውበትን ለማረጋገጥ በመንግስ በኩል ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ውጤታማ ስራ፣ የተቀናጁ የጎርፍ መከላከያ ሥርዓቶችን፣ በአስደናቂ የሥነ-ሕንጻ ጥበብ የተገነቡ ዘመናዊ ድልድዮችን እና ሰፋፊ አረንጓዴ የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎችን አካቷል።

ፕሮጀክቱ ወንዙን እና የወንዙን ዳርቻ ማራኪ የአይን እና የመንፈስ ምግብ በማድረግ፤ መዲናዋን ለኑሮ ተስማሚ እና የአየር ንብረትን በመቋቋም ረገድ አይነተኛ ተምሳሌት የሆነች ዓለም አቀፍ የቱሪዝም እና የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በስኬት ጎዳና ላይ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

አዲስ አበባ በአሁኑ ወቅት በፍጥነት በማደግ እና በመዘመን ላይ የምትገኝ አፍሪካዊት የኩራት ምንጭ እየሆነች መምጣቷን መዲናይቱን በተለያዩ አጋጣሚዎች የጎበኙ የዓለማችን ታዋቂ ሰዎች ምስክርነታቸውን እየሰጡ ነው።

በዚህ ከተማዋን አዲስ፣ ማራኪ፣ ምቹ እና ተወዳዳሪ ገጽታ ለማላበስ እየተከናወኑ ያሉ የወንዝ ዳርቻ የልማት ተግባራት እንደ ቀበና ወንዝ ያሉ ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ መዳረሻዎች የቀደመ ግርማ ሞገሳቸውን ሳያጡ፣ የትዝታ ማህደራቸውን እንዳነገቡ ከመዲናይቱ አዲስ መልክ ጋር ተሸምነው የነገ የጋራ ተስፋ ቀንዲል እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡

ዛሬ ቀበና ተፈጥሯዊ ግርማውን እንደጠበቀ ዘመኑ በደረሰበት የኪነ ህንጻ ቴክኖሎጂ ተከሽኖ አዲስ አበባ የደረሰችበትን የግስጋሴ ደረጃ የሚያበስር ታላቅ የቱሪዝም ኃውልት ሆኗል።

ለመዲናይቱ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን፣ ለዓለም አቀፍ ጉባኤዎችና ለጉብኝት ወደ መዲናዋ ለሚጎርፉ ዓለም አቀፍ እንግዶችና ዲፕሎማቶችም ውብ እና አስደናቂ መዳረሻ ሆኗል፡፡

ታሪካዊ እሴቱን ከወደፊቱ ራዕይ ጋር አጣጥሞ በመጓዝ፣ የቀበና ወንዝ ነባር ክብሩን ጠብቆ፣ አሁናዊ ውበትን አጥብቆ፣ ቀጣይ የመዲናይቱን ራዕይ ሰንቆ ትውልዱ ለሚናፍቃት የነገዋ ኢትዮጵያ ቅድመ መልክ ሆኗል፡፡

በምሕረት ደምሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.