የባህር በር – ትልቁ ሀገራዊ የቤት ስራ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ለብዙ የዓለም ሀገራት የባህር ውሃ በቀላሉ የሚገኝ የተፈጥሮ ስጦታ ቢሆንም፣ ለኢትዮጵያ ግን በየዓመቱ ቢሊየን ዶላሮችን እንድታወጣ የሚያስገድዳት ምክንያቷ ሆኗል።
ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ወደብ አልባ ከሆነችበት ጊዜ አንስቶ ከሶስት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ይህ እውነታ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት እና በትውልዱ ስነ-ልቦና ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊየን በላይ የህዝብ ቁጥር ይዛ የባህር በር የሌላት ግዙፍ ሀገር ሆና ዓመታትን በከባድ ጫና ውስጥ አሳልፋለች።
ይህ የታሪክ እና የጂኦግራፊ አጋጣሚ ኢትዮጵያን በየዓመቱ እያስከፈላት ያለው ዋጋ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የዘርፉ ተንታኞች ይገልጻሉ።
የኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ ከ95 በመቶ በላይ የሚንቀሳቀሰው በጎረቤት ሀገር ወደብ በኩል በመሆኑ ለዚህ አገልግሎት በየዓመቱ የሚከፈለው ከፍተኛ የኪራይ እና የሎጂስቲክስ ወጪ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ አቅም በእጅጉ እየፈተነው ይገኛል።
የወጪ ንግድ ዋጋን መቀነስ፣ እጥረት ያለበትን የውጭ ምንዛሪ ማዳን እና በዜጎች ላይ የተጫነውን የኑሮ ውድነት ማቃለል የሚቻለው ይህ የስትራቴጂካዊ ኮሪደር ጥያቄ ዘላቂ ምላሽ ሲያገኝ ነው።
የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ጥያቄ የድንበር ወረራ ወይም የሌሎችን ሉዓላዊነት የመንካት ፍላጎት የሌለው፣ ይልቁንም የጂኦፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ህልውናን ያካተተ ብሎም ከቁጥር ባለፈ የትውልድ ስነ-ልቦናዊ መታፈንን የመቅረፍ ጉዳይም ጭምር ነው።
ኢትዮጵያ ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የምትከተለው መንገድ በኃይል ሳይሆን በዲፕሎማሲ ላይ የተመሰረተ ነው።
የጋራ ልማት፣ የጋራ ተጠቃሚነት እና የንግድ ልውውጥን መሰረት ባደረገ የሰላም መንገድ አማራጭ የሌለው መፍትሄ መሆኑን መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።
ከዓለም አቀፍ የባህር ህግጋት አንጻርም የተባበሩት መንግስታት የባህር ህግ ኮንቬንሽን (ዩኤንሲኤልኦኤስ) አንቀጽ 125፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደብ አልባ ሀገራት ከዓለም ጋር ለመገናኘት የጎረቤት ሀገራትን ግዛት በነጻነት የመሸጋገር እና ወደቦችን ያለ አድልዎ እኩል የመጠቀም ህጋዊ መብት እንዳላቸው ይደነግጋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በምታደርጋቸው ጥረቶች ለጥያቄዋ መልስ ለማግኘት አሁን ላይ የምትፈልገው የነገ ቀጠሮ ሳይሆን የዛሬ ቁርጠኝነት ነው።
ለዚህ ታሪካዊ ርምጃና ሀገራዊ ግብ መሳካት ደግሞ መላው ዜጋ በአንድነትና በቁርጠኝነት ሊቆም ይገባል።
በሶስና አለማየሁ