በመዲናዋ የ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች ከ97 በመቶ በላይ ወደ ቀጣዩ ክፍል ተዛውረዋል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በመዲናዋ የ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች 97 ነጥብ 48 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወደ ቀጣዩ ክፍል ተዛውረዋል አሉ።
ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፤ ዘንድሮ 84 ሺህ 257 ተማሪዎች ፈተናውን ወስደው 82 ሺህ 137 ተማሪዎች 50 በመቶ እና በላይ ውጤት አስመዝግበዋል ብለዋል።
የተመዘገበው ውጤት በ2017 ዓ.ም ከነበረው 95 በመቶ አንጻር እድገት ማሳየቱን ገልጸው፤ ለውጤቱ መሻሻል አስተዋጽኦ ላደረጉ ባለድርሻዎች ምስጋና አቅርበዋል።
ዘንድሮ ከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ስራዉ ልዩ ትኩረት በመስጠት መንቀሳቀሱ፣ የትምህርት ቤት ምገባ መርሀ ግብር ተጠናክሮ መቀጠሉ እና የሂሳብና እንግሊዘኛ ትምህርት ስትራቴጂ ተነድፎ በትኩረት መስራት መቻሉ ለውጤቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል።
በተጨማሪም የመማሪያና የማስተማሪያ ግብዓቶች መቅረባቸው እንዲሁም ከትምህርት ባለድርሻ አካላት ጋር በተለይም ከወላጆች ጋር በቅንጅት መሰራቱ የጎላ ሚና እንደነበራቸው አብራርተዋል።
በከተማ አስተዳደሩ በትምህርት ስርዓቱ የብዝሀ ቋንቋ ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ አማርኛ እና አፋን ኦሮሞ እንደሁለተኛ ቋንቋ የተማሩ ተማሪዎች በትምህርት አይነቶቹ ፈተና መውሰዳቸውን አስታውሰዋል።
የ6ኛ ክፍል ከተማ አቀፍ ፈተናን ካስፈተኑ 768 ትምህርት ቤቶች መካከል 543 ያህሉ ተማሪዎቻቸውን ሙሉ በሙሉ ማሳለፋቸውን ጠቁመዋል።
ተፈታኝ ተማሪዎች ከታች የተቀመጠውን ሊንክ በመጠቀም ከዛሬ ጀምሮ ውጤታቸውን ማየት እንደሚችሉ በጋዜጣዊ መግለጫው ተጠቁሟል።
https://aa6.ministry.et/#/result