የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የኤሌክትሪክ ገበያን ለማስጀመር…
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ ኃይል ትስስር አባል ሀገራት የኤሌክትሪክ ገበያ ወደ ሥራ እንዲገባ ጥሪ አቅርባለች።
37ኛው የምስራቅ አፍሪካ ኃይል ትስስር ስቲሪንግ ኮሚቴ ልዩ ስብሰባ በአዲስ አበባ በዛሬው ዕለት መካሄድ ጀምሯል፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴዔታ ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ÷ ኢትዮጵያ በቀጣናው የኃይል ትስስርን ለማሳለጥ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ ኃይል ትስስር አባል ሀገራት የቀጣናውን የኤሌክትሪክ ገበያ በአስቸኳይ ወደ ሥራ እንዲያስገቡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ተጨማሪ መዘግየቶች ከድንበር ተሻጋሪ የኤሌክትሪክ ንግድ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊና ልማታዊ ጥቅም እያሳጡ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በቅርብ ዓመታት የምስራቅ አፍሪካ ኃይል ትስስር ገለልተኛ የቁጥጥር ቦርድ ሴክሬታሪያት በዩጋንዳ መቋቋሙን እንዲሁም ትስስሩ ያስመዘገበውን ከፍተኛ እድገት አድንቀዋል።
የስቲሪንግ ኮሚቴው ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሸብር ባልቻ (ኢ/ር) በበኩላቸው ÷ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከፍተኛ የውሃ፣ የጂኦተርማል፣ የንፋስ እና የፀሐይ ኃይል ሃብቶች መኖራቸውን አውስተዋል፡፡
ይሁን እንጂ በአካባቢው የሚገኙ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች አሁንም አስተማማኝና ተመጣጣኝ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደማያገኙ ነው ያስረዱት፡፡
ክልላዊ የኃይል ትስስር የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት፣ የኃይል ደህንነትን ለማረጋገጥ፣ የኤሌክትሪክ ዋጋን ለመቀነስና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን እውን ለማድረግ ውጤታማ መንገድ ነው ማለታቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል፡፡
የኤሌክትሪክ ገበያን ለመጀመር የሚያስፈልጉ ቴክኒካል ዝግጅቶች ከአንድ ዓመት በፊት ቢጠናቀቁም ገበያው እስካሁን ወደ ንግድ ሥራ አለመግባቱ አሳሳቢ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ስብሰባው በኮሚቴው የቀጣይ አስተዳደር እና ክልላዊ የኤሌክትሪክ ገበያን ወደ ሥራ ለማስገባት ለ22ኛው ልዩ የሚኒስትሮች ም/ቤት የሚቀርቡ ምክረ ሀሳቦችን እንደሚያዘጋጅ ይጠበቃል።