የቅራኔዎች ሐኪም …
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራት በየዘመናቱ ያስተናገዷቸው ቀውሶች በአንድም በሌላ መልኩ ከተሳሳተ ትርክት ጋር የተያያዙ ናቸው። ከፋፋይ ትርክቶች፣ አካባቢያዊ እና እጅግ አሳሳች ለሆኑ ትረካዎች ሰለባ ያደርጋሉ።
እነዚህ የታሪክ ቅንጥብጣቢዎች በደሎች ላይ ብቻ የሚያተኩሩ ፍርሃቶችን የሚያጎሉ እና አንዱን አሸናፊ ሌላውን ተሸናፊ በማድረግ የሚስሉ ናቸው፡፡
እነዚህ የተበታተኑ ታሪኮች የበላይነት ሲይዙ፣ የሕዝብ እምነት ይሸረሸራል፤ ትናንሽ አለመግባባቶችም በፍጥነት ወደ ሰፊ የሰላም እጦትና አለመረጋጋት ይቀየራሉ።
ይህን አዙሪት ለመስበር፣ ሀገር ከፖሊሲ ለውጦች በላይ የሆነ መላ ያስፈልጋታል፤ ይህም ከተሳሳተ አተራረክ ወደ የጋራ ታሪክ መሻገርን ይጠይቃል።
ይህም ልዩነትን መደምሰስ ወይም ጥያቄዎችን ማፈን ሳይሆን ልዩ ልዩ ተሞክሮዎችን ወደ አንድ ወጥ እና የተቀናጀ ብሔራዊ ማንነት ማሳደግ ነው፡፡
የችግሮች መሰረት የሆነው የተዛነፈ ትርክት የፈጠረውን ስብራት በሕግ እና መመሪያዎች ብቻ መጠገን አይቻልም፤ ገለልተኛ መድረክ እና የጋራ ምክክርን ይጠይቃል።
ኢትዮጵያ የመረጠችው መንገድም ይኸው ነው፡፡ ምክክር ቅራኔዎችን ወደ ገንቢ እና አግባቢ ውሳኔዎች ይቀይራል። በጠረጴዛ ዙሪያ መደራደር ለጥያቄዎች ምላሽ ያስገኛል።
ምክክር የከረሙ እና በድንግዝግዝ ሲብላሉ የኖሩ አሳሳች ትረካዎች ጸሐይ እንዲሞቃቸው አለመረጋጋትን የሚቀሰቅሱ ሆን ተብለው የተፈጠሩ ፍርሃቶች በምክንያታዊነት እንዲታረሙ እድል ይፈጥራል፡፡
በሀገር ውስጥም ይሁን በውጭ ሀገር ከሚገኙ የተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ሲደረግ የቆየው ውይይትና ምክክርም የዴሞክራሲ ምሕዳሩን ለማስፋት እና ሀገራዊ መግባባትን እውን ለማድረግ ወሳኝ ርምጃ ተደርጎ የሚወሰደው ለዚህ ነው።
አማራጭ አመለካከቶች በጦር ሜዳ ሳይሆን በሃሳብ አደባባይ እንዲፈተኑ በማድረግ የፖለቲካ ሥልጣን መመንጨት ያለበት ከሰላማዊ የሕዝብ ውሳኔ መሆኑን በመርህ ያረጋግጣል።
በአሁኑ ወቅት በዋዜማው ላይ የሚገኘው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሰላም አማራጮች ጋር ተዳምሮ ለብሔራዊ መግባባት ቀና መንገድ ይከፍታል።
ቅራኔዎችን በውይይት በማከም እና ከፋፋይ ትርክትን በጋራ ሀገራዊ ራዕይ በመተካት፣ ጠንካራ እና ሰላማዊ ዋስትናዋ የተረጋገጠ ሀገር መገንባት ይቻላል፡፡
በምሕረት ደምሴ