ብዝኀ ዘርፍ ኢኮኖሚ …
ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የመደመር እሳቤ፤ ከነጠላ ዘርፍ ጥገኝነት ተላቅቃ ወደ ዘርፈ-ብዙ የኢኮኖሚ ስርዓት እየተሸጋገረች ትገኛለች፡፡
የብዝኀ ዘርፍ ኢኮኖሚ አንዱና ዋነኛው ጥንካሬ የዘርፎች መደመር ነው። የግብርናው ዘርፍ ለኢንዱስትሪው የጥሬ እቃ ግብአት በማቅረብ፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እሴት በመጨመር፣ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉ ምርቱን ለገበያ በማድረስ በጋራ ይመጋገባሉ፡፡ ይህ የጋራ ትስስርና የመደመር እሳቤ የሀገር ውስጥ አቅምን ከፍ በማድረግ የተኪ ምርት አቅምን እያሳደገው ነው፡፡
በኢኮኖሚ ውስጥ የነጠላ መስኮች የበላይነት እየቀነሰ በመምጣቱ፤ የግሉ ክፍለ-ኢኮኖሚ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ሰፊ አጋጣሚዎችን እያገኘ ነው፡፡ አዲሱ የምጣኔ ኃብት የመደመር እሳቤ የተለያዩ መስኮች ራሳቸውን ችለው ለሀገር ኢኮኖሚ አመርቂ ውጤት እንዲያመጡ አስችሏል፡፡
የተለያዩ ዘርፎችን በአንድ ላይ ማስተሳሰር ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የስራ እድል በመፍጠር ለኑሮ መሻሻል ምክንያት እየሆነ ይገኛል፡፡ በተለይም ወጣቶችና ሴቶች በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ እና በቱሪዝም ዘርፎች ሰፊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ ይገኛሉ፡፡
ኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ከማዘመን ጎን ለጎን፤ ኢንዱስትሪን፣ ማዕድን ማውጣትን እና ቱሪዝምን እንዲሁም የዲጂታል አብዮትን በማስፋፋት የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ሞተር በማድረግ በርካታ ስኬቶችን አስመዝግባለች።
መንግሥት የኢኮኖሚውን አቅም በማሳደግ፣ ስጋቶችን ወደ እድል በመቀየር ለውጭ እና ሀገር ውስጥ ጫናዎች የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት ችሏል። በተጨማሪም የቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት የሀገሪቱን ገጽታ በመቀየር የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትና አዳዲስ የስራ እድሎችን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ድርሻ አበርክቷል::
በአጭሩ የብዝኀ ዘርፍ ኢኮኖሚ የሀገርን ምጣኔ ሀብት ዘላቂና አካታች መሠረት እንዲኖረው የሚያደርግ ቁልፍ ስትራቴጂ ነው፡፡ ከአንድ ነጠላ ዘርፍ ወጥቶ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝም እና በአገልግሎት እንዲሁም በአይሲቲ ዘርፎች ላይ መደገፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ፈጣንና ፍትሃዊ የኢኮኖሚ እድገት እንዲያስመዘግቡ ያስችላቸዋል፡፡