የባህር በር ተደራሽነት፡ የኢትዮጵያ የልማት ቁልፍ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህር በር ተደራሽነት በዘመናችን ከኢኮኖሚ እድገት፣ ከብሔራዊ ደህንነት፣ ከንግድ እና ከክልላዊ ትስስር ጋር በጥብቅ የተያያዘ ጉዳይ ሆኗል።
በተለይም ከ120 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ላላት ኢትዮጵያ የባህር በር ተደራሽነት የቀን ፖለቲካ ክርክር ሳይሆን የረጅም ጊዜ የልማት ስትራቴጂ ሊሆን ይገባዋል።
ለብዙ ዘመናት ከቀይ ባህር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የነበራት ኢትዮጵያ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ባልተገባ መንገድ ተገፍታ የባህር በር አልባ ለመሆን ተገድዳለች።
ከዚያ ወዲህ አብዛኛው የውጭ ንግዷን በጎረቤት ሀገሮች ወደቦች፣ በተለይም በጅቡቲ ወደብ ትጠቀማለች።
ይህ ሁኔታ የንግድ ወጪ እንዲጨምር፣ የሎጂስቲክስ ፈተናዎች እንዲፈጠሩ እና በአንድ ዋና የመጓጓዣ መስመር ላይ ከፍተኛ ጥገኝነት እንዲኖር አድርጓል።
በዓለም አቀፍ ሥርዓት የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት በአክብሮት የሚጠበቅ ሲሆን፤ ባህር የሌላቸው ሀገራትም በስምምነትና በሕጋዊ መንገድ ወደ ባህር የመድረስ መብቶችን የሚያገኙበት ዕድል አለ።
በባህር በር ጉዳይ ከሁለት አንጻር የሚታይ ሲሆን፤ እነሱም የ”ባለቤትነት” እና የ”ተደራሽነት” ጽንሰ ሐሳቦችን ናቸው።
የባህር በር ባለቤትነት ከአንድ ሀገር ሉዓላዊ ግዛት ጋር የተያያዘ ሲሆን የባህር ተደራሽነት ግን ባህር የሌላት ሀገር በዓለም አቀፍ ሕግና በሁለትዮሽ ወይም በክልላዊ ስምምነቶች መሠረት ወደ ባህር የምትደርስበትን መብት ያመለክታል።
ስለዚህ ዋናው ጥያቄ “ባህሩ የማን ነው?” የሚለው ሳይሆን፣ “ኢትዮጵያ ዘላቂ፣ አስተማማኝ፣ ወጪ ቆጣቢ እና ሕጋዊ የባህር ተደራሽነትን እንዴት ታረጋግጣለች?” የሚለው ነው።
ኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዋን ለማሳደግ፣ የግብርና ምርቶቿን ወደ ውጭ ገበያ በተወዳዳሪ ዋጋ ለማቅረብ፣ የማዕድን ሀብቷን ለማልማት እና የውጭ ንግዷን ለማስፋፋት ቀልጣፋ እና ውጤታማ የባህር መዳረሻ ያስፈልጋታል።
የመጓጓዣ ወጪ በቀነሰ መጠን የምርት ዋጋ ይቀንሳል፤ የኢንቨስትመንት ፍላጎት ይጨምራል፤ የሥራ ዕድሎች ይፈጠራሉ፤ የውጭ ምንዛሬ ገቢም ያድጋል። በዚህ መልኩ የባህር በር ተደራሽነት የልማት አስፈላጊ መሠረት ይሆናል።
በሌላ በኩል ለባህር በር ተደራሽነት ቀጣናዊ ትብብር ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡
በዚህም የአፍሪካ ቀንድ ከጂኦፖለቲካዊ አቀማመጡ የተነሳ በዓለም የንግድ መስመሮች ውስጥ ከፍተኛ ስትራቴጂያዊ ዋጋ አለው። ይህን አቅም ወደ ዘላቂ እድገት መቀየር የሚቻለው በፉክክር ሳይሆን በትብብር ነው።
ወደቦችን፣ የባቡር መስመሮችን፣ የመንገድ አውታረ መረቦችን፣ የኃይል ትስስሮችን እና የንግድ ኮሪደሮችን በጋራ ማልማት ለሁሉም ሀገራት ተጠቃሚ የሆነ የጋራ እድገትን ያመጣል።
የተረጋጋ ሰላም እና የንግድ ነጻነት ካለ የባህር በር ጥያቄም ከግጭት ይልቅ በጋራ ጥቅም መንፈስ የማይመለስበት ምንም ምክንያት የለም፡፡
ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባህር ተደራሽነትን ማግኘት የልማቷ አስፈላጊ አካል ሲሆን በተመሳሳይ የጎረቤት ሀገራት ሉዓላዊነትና ደህንነት መከበር የክልሉ መረጋጋት መሠረት ነው።
ስለሆነም የወደፊቱ አቅጣጫ ግጭትን ሳይሆን ድርድርን፣ ፉክክርን ሳይሆን ትብብርን፣ አንድን ወገን ማሸነፍን ሳይሆን የጋራ ብልጽግናን ያበረታታል።
በአመለወርቅ ደምሰው