የአውሮፓ ህብረት ለኢጋድ አባል ሃገራት 60 ሚሊየን ዩሮ የሚያወጡ የኮሮና ቫይስ መከላከያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአውሮፓ ህብረት ለምስራቅ አፍርካ ሀገራት የልማት በየነ መንግስታት (ኢጋድ) አባል ሀገራት 60 ሚሊየን ዩሮ የሚያወጡ የኮሮና ቫይስ መከላከያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉ ሙሉ በሙሉ ሃገራቱ ኮቪድ 19ኝን ለመከላከል ለሚያደርጉት እንቅስቃሴና ፕሮግራም የሚውል ሲሆን፥ ለኢጋድ አባል ሀገራት በኢትዮጵያ በኩል እንዲደርስ ዛሬ ርክክብ ተደርጓል።
የኢጋድ ዋና ጸሃፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በርክክብ መርኃግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር የአውሮፓ ህብረት ለኢጋድ አባል ሃገራት ያደረገው ድጋፍ በመከላከል ሂደቱ ማህበረሰቡን ከሞት ከመታደግ ባለፈ ተጋላጭ ለሆኑት የህክምና ባለሙያዎችም የደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ስነ ስርዓት ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ተገኝተዋል።
ድጋፉ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች በተለይም ለሀገር ውስጥና የውጭ ተፈናቃዮች እንዲሁም ለስደተኞች የሚውል እንደሚሆንም ህብረቱ አሳውቋል።
በዚህ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰርጂካል ማስክ፣ 24 አምቡላንሶች፣ 8 ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪዎችና 70 ሺህ መመርመሪያዎችን በማቅረብ በምስራቅ አፍሪካ ስኬታማ የኮሮና ቫይረስ የመከላከል ስራ ተግባራዊ እንዲሆን የበኩሉን ድጋፍ አድርጓል።
ፕሮግራሙ ከአጋር ሃገራት ባለፈ ዓለም አቀፍ የሕፃናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ )፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፕሮጀክት አገልግሎት ፅህፈት ቤት፣ የጀርመን የልማት ኤጀንሲ፣ በአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት እና በምስራቅ አፍሪካ የንግድ ምልክት( Trade Mark east Africa) በተባሉት አጋር ድርጅቶች ቅንጅት ለኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳንና ዩጋንዳ ተግባር ላይ የሚውል ይሆናል ተብሏል።
ድጋፉ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑት የህብረተሰብ ክፍል የሚውሉ 8 ነጥብ 5 ሚሊየን የቫይረሱ መከላከያ ቁሳቁሶችን ያካተተ ነው።
የህብረቱ ዓለምአቀፍ አጋርነት ኮሚሽነር ጁታ ኡርፒላይነን ለስምንቱ የኢጋድ አባል ሀገራት የተደረገው ድጋፍ ቫይረሱን በተቀናጀና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመከላከል ለሚደረገው ድጋፍ ሁነኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው እምነታቸው መሆኑን ነው የተናገሩት።
በአክሱማዊት ገብረህይወት
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።