የሕጻናትን መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ – ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕጻናትን መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚከናወኑ ሁሉ አቀፍ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ አሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)።
‘‘የተጠበቁ ሕጻናት ለበለፀገ ትውልድ’’ በሚል መሪ ሃሳብ የአፍሪካ ሕጻናት ቀን ማጠቃለያ ፕሮግራም በሐረር ከተማ ተካሂዷል።
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት ÷ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለነገ ሀገር ተረካቢ ህጻናት አስፈላጊው መሰረተ ልማቶች የማሟላት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በተለይም ውብ፣ ምቹና ጽዱ የመዝናኛ እንዲሁም የሕጻናት ማቆያና መንከባከቢያ ማዕከላትንና የመጫወቻ ስፍራዎችን የመገንባትና የማስፋፋት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን የሕጻናት ድጋፍና እንክብካቤ፣ በተለያዩ ዘርፎች ተሳትፏቸውን የማጎልበት እንዲሁም በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተጎጂ እንዳይሆኑ የመጠበቅ፣ ከጥቃት የመከላከልና ሌሎች በርካታ ስራዎችም መከናወናቸውን አንስተዋል።
የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ሕጻናትን መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከማሕበረሰቡና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሚከናወኑ ሁሉ አቅፍ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።
የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር በበኩላቸው÷ በክልሉ በከተማም ሆነ በገጠር ያሉ ህጻናት መብት፣ ደህንነትና ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ የልማት ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
የሕጻናት ሁለንተናዊ እድገት ስኬታማ የሚሆነው በመንግስት ጥረት ብቻ አለመሆኑን ጠቁመው በክልሉ በገጠርና በከተማ ያሉ ህጻናት እኩል ተጠቃሚና ተደራሽነትን ለማጎልበት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎን ማጎልበት እንደሚገባ መጠቆማቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል፡፡