አረንጓዴ ዐሻራ ለስነ ምህዳር መታደስ ጉልህ አስተዋፆኦ እያደረገ ነው – ለሊሴ ነሜ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ በማልማት የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ እንዲፈጠር አስችሏል አሉ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ለሊሴ ነሜ (ዶ/ር)፡፡
ለሊሴ ነሜ (ዶ/ር) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር አካባቢን ከብክለትና ከዕፅዋት መራቆት የምንጠብቅበት ነው ብለዋል።
መርሐ ግብሩ የተዛባው የተፈጥሮ ሚዛን የሚስተካከልበት ዋና መንገድ መሆኑን ገልጸው፤ አረንጓዴ ዐሻራ ለስነ ምህዳር መታደስ ጉልህ አስተዋፆኦ እያደረገ ነው ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ የአየር ብክለትን ለመቀነስና ለቀጣዩ ትውልድ ምቹና አረንጓዴ ሀገርን ለማስረከብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አመልክተዋል።
የአረንጓዴ ዐሻራና ሰው ሠራሽ ደን ሥራ አስፈጻሚ አበሩ ጠና በበኩላቸው፤ በመርሐ ግብሩ የተተከሉ ችግኞች ከአካባቢ ጥበቃ ባሻገር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም እያስገኙ ነው ብለዋል።
መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳ ያላትን ዓለም አቀፍ አስተዋጽኦ በማጉላት ለካርቦን ገበያ ተጠቃሚነትም ምቹ መሠረት እየፈጠረ መሆኑን ጨምረው አብራርተዋል።
ይህ መርሐ ግብር በተለይ ሀገር በቀል ዕፅዋትን በማስፋፋት የሥነ-ምህዳር ሚዛንን ለመጠበቅ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሆነም መመላከቱን ኢዜአ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቋቋም፣ የደን ሽፋኗ ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችለውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተገበረች ነው።
በመርሐ ግብሩ እስካሁን ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፤ ዘንድሮ “ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ሐሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ ስምንት ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል።