ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያጋራችው ትልቅ ተሞክሮ …
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥ ፈጣን እና አሳሳቢ መዘዞችን እያመጣ ባለበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ታሪካዊ የሆነውን የደን መመናመን ለመቀልበስ ግዙፍ አረንጓዴ ምዕራፍ ከፍታለች።
የ”አረንጓዴ ዐሻራ” መርሐ ግብር ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ በቢሊየን የሚቆጠሩ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን የደን፣ የፍራፍሬ፣ የመኖና ሌሎች ፋይዳ ያላቸውን ዛፎችን በመትከል እዚህ ደርሷል።
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች ተተክለው ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ ያስቻለ ውጤት ተገኝቷል።
መርሐ ግብሩ ከችግኝ ተከላ ዘመቻነት ተሻግሮ ሀገሪቱን ወደ አዲስ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና የዲፕሎማሲ ከፍታ እያሸጋገራት ይገኛል።
ዛፍ መትከል የሕልውና ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በቢሊየኖች የሚገመት የካርበን ፋይናንስ እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድሎችን የሚከፍት የልማት ስትራቴጂ ሆኗል።
መርሐ ግብሩ ከችግኝ ተከላ የዘለለ ግዙፍ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ትርጉም በመሰነቅ እየተተገበረ መሆኑን አሳይቷል።
ዓለምን እየፈተነ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ጫና ለመቋቋም የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከት የጀመረ ሲሆን፤ የሀገሪቱን የደን ሽፋን 23 ነጥብ 6 በመቶ በማድረስ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ የሙቀት አማቂ ጋዞችን የመያዝ አቅምን አሳድጓል።
ይህም ኢትዮጵያ በካርቦን ሽያጭ የምታገኘውን ገንዘብ በማሳደግ የሀገር ኢኮኖሚን መደገፍ ጀምሯል።
የሚተከሉት ቢሊየን ዛፎች ከፍተኛ መጠን ያለው ካርበን ከከባቢ አየር ውስጥ ይመጥጣሉ፤ በካይ ሀገራት ደግሞ ለዚህ የተፈጥሮ ውለታ ክፍያ በመፈጸም የካርበን ግብይት ያካሂዳሉ።
ኢትዮጵያ በካርበን ግብይት ተጨባጭ ስኬት ያስመዘገበች ሲሆን፤ ደን ያለባቸው የተለያዩ አካባቢዎች ማህበረሰቦች ከዚህ የካርበን ግብይት ስርዓት ተጠቃሚ መሆን ጀምረዋል።
በተጨማሪም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ሂደትን በማሳለጥ የራሱን ሚና እየተወጣ ሲሆን፤ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃን እያጠናከረ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ችግኝን እንደ ዲፕሎማሲያዊ መሣሪያ እየተጠቀመችበት ሲሆን፤ ለጎረቤት ሀገራት በሚሊየን የሚቆጠሩ ችግኞችን በነጻ በማካፈል የቀጣናውን አረንጓዴ ልማት ለማጠናከር የድርሻዋን እየተወጣች ነው።
የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ጸድቀው ዛፍ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ ኅብረተሰቡ የችግኞቹ ቀጥተኛ ጠባቂ እና ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሠራር ማጠናከር እና የካርበን ሽያጭ ተቋማዊ አሠራሮችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማገዝ፣ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ፋይናንስ ተገቢውን ክፍያ እንድታገኝ አጠናክሮ መሥራት ከባለድርሻዎች ይጠበቃል።
በአጠቃላይ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ከተፈጥሮ ጋር ያላትን ቁርኝት ወደ ዘመናዊና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረትነት የቀየረችበት ስኬታማ ጉዞ ነው።
ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል፣ ከካርበን ሽያጭ ተጠቃሚ በመሆን እና ለጎረቤት ሀገራት አረንጓዴ ስጦታዎችን በማበርከት ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትልቅ ተሞክሮ አጋርታለች።