አፈርሳታ እውነት አደባባይ የምትወጣበት …
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጥንታዊት ኢትዮጵያ በባህላዊ መንገድ ወንጀሎችን ለማጣራት ጥቅም ላይ የሚውል ነባር ሀገር በቀል እውቀት ነው አፈርሳታ።
በአንዳንድ አካባቢዎች አውጫጪኝ በሚል ስያሜ የሚታወቀው ይህ የምርመራ ስርዓት ጥፋተኞችን ለማውጣጣት ነዋሪዎች በዛፍ ጥላ ስር የሚሰባሰቡበት መድረክ ነው።
አፈርሳታ ንብረት የጠፋው ሰው የገጠመውን ጉዳይ ለአካባቢው ባህላዊ መሪዎች ወይም ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በማስረዳት ግፍ የፈጸመበት ሰው እንዲገኝለት እና ፍትህ እንዲሰጠው የሚጠይቅበት ሀገር በቀል ዕውቀት ነው፡፡
ለምሳሌ በአንድ አካባቢ ፈረስ፣ በሬ፣ ወይም ሌላ የቤት እንስሳ አሊያም ንብረት ከጠፋ ይህን እኩይ ተግባር የፈጸመውን ግለሰብ ለማግኘት የአካባቢው ነዋሪ ይሰበሰባል።
እዚህ አካባቢ ማን ነበር ከማን ጋር ታይቷል ምን አይነት አጠራጣሪ ተግባር ሲፈጽም ተስተውሏል የሚሉ እና የመሳሰሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ።
በግልፅ የማጣሪያ መንገዶች ተመርምሮ ጥፋተኝነቱ የተረጋገጠ ወንጀለኛ ላይ የፍርድ ውሳኔ የሚሰጥበት ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ነው፡፡ አፈርሳታ፡፡
የወሰደውን ጊዜ ይውሰድ እንጂ በአፈርሳታ ስርዓት ላይ የታደመ የአካባቢው ነዋሪ እውነቱ ሳይወጣ የትም ንቅንቅ አይልም፡፡
በየቤቱ የቡና ማጣጪያ የነበረ ሃሜት የሚያከትምበት እና አሉባልታ የሚጠራበት የእውነት ምንጭም ነው፡፡
አፈርሳታ በነዋሪዎች መካከል መተማመንን ለማስፈን እና የማህበረሰብ ሰላም እና አንድነትን የሚያጸና ትውፊት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ችግሮቿን ሁሉ ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሷ በመፍታት በዘመናት ያጋጠሟትን ተግዳሮቶች በድል ተሻግራ ዛሬ ላይ ለመድረሷ አብነት ሆነው ከሚያገለግሉ እድሜ ጠገብ ክዋኔዎች መካከል አፈርሳታ ቀዳሚው ነው።
ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሁሉንም የማህበረሰብ አካል በፍትሃዊነት እና በእኩልነት የሚያስተናግድ አንዱን በተለየ የማያቅፍ ሌላውን በአድልዎ የማይገፋ አካታች ባህላዊ አስተዳደር ነው አፈርሳታ።
ዛሬ ኢትዮጵያ ዘመናትን የተሻገሩ ችግሮቿን በልጆቿ አማካይነት ወደ አደባባይ አምጥታ በውይይት ለመፍታት የምታካሂዳቸው ተግባራት ድንገት የበቀሉ ሳይሆን እንደ አፈርሳታ ባሉ ነባር ክዋኔዎች ላይ የተመረኮዙ መሆናቸውን ያመላክታል፡፡
እንደ ሀገር ብዙ አደባባይ ላይ ያልወጡ ነገር ግን ለአለመግባባት፣ ለጥርጣሬ እና ለግጭቶች መነሻ የሆኑ ማህበረሰባዊ ጭምጭምታዎችና ውዥምብሮች የአፈርሳታ አይነት ልየታና ምክክር ተደርጎባቸው የእርቅ ፀሐይ እንዲሞቃቸው ሊደረግ ግድ ይላል።
በምሕረት ደምሴ