Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ በኢራን ሦስተኛ ዙር ጥቃት ስትፈጽም፤ ኢራን የአጸፋ ርምጃ መውሰዷን አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ ዛሬ ሌሊት በኢራን ላይ ሦስተኛ ዙር ጥቃት ስትፈጽም፤ ቴህራን በምላሹ በቀጣናው የሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮችን ኢላማ ማድረጓን አስታውቃለች፡፡
የአሜሪካ ጦር ማዕከላዊ እዝ (ሴንትኮም) ኢራን በሆርሙዝ ሰርጥ በማለፍ ላይ በነበረው የቆጵሮስ የእቃ ጫኝ መርከብ ላይ ጥቃት ፈጽማለች ሲል ወንጅሏል፡፡
ማዕከላዊ እዙ ባወጣው መግለጫ በጥቃቱ የመርከቧ አካል መቃጠሉንና የመርከቧ ሲቪል ሰራተኛ መሰወሩን ጠቅሶ፥ በዚህም ጉዞዋን መቀጠል እንዳልቻለች አመልክቷል፡፡
የአሜሪካ ጦር ጥቃቱን ተከትሎ በወሰደው ሦስተኛ ዙር ወታደራዊ ርምጃ የኢራን የሚሳኤል፣ የባህር ኃይል እና የድሮን ጣቢያዎችን ጨምሮ 140 ኢላማዎችን መምታቱን አስታውቋል፡፡
ኢራን በምላሹ የኳታር የአል ኡዴይድ የአየር ኃይል ጣቢያን ጨምሮ በባህሬን፣ ኩዌት እና ጆርዳን በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች ላይ የአጸፋ ጥቃት መፈጸሟን አስታውቃለች፡፡
የኢራን አብዮታዊ ዘብ ዛሬ ንጋት ላይ በጆርዳን በሚገኝ የአሜሪካ የጦር ሰፈር ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ እና የድሮን ማከማቻን ጨምሮ ቁልፍ ኢላማዎችን መምታቱን ገልጿል፡፡
ስምምነቱን በመጣስ እርስ በእርስ እየተወነጃጀሉ የሚገኙት አሜሪካ እና ኢራን ለሚቃጣባቸው ጥቃት የአጸፋ ርምጃዎችን እንደሚወስዱ ማስጠንቀቃቸውን ተከትሎ በቀጣናው ያለው ውጥረት ተባብሶ መቀጠሉን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በመልካም ፈቃዱ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.