የልብ ህሙማንን ሕይወት ለመታደግ ከፋውንዴሽኑ ጋር ለመስራት ተስማምተናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የልብ ህሙማንን ሕይወት ለመታደግ ከኸርት አታክ ኢትዮጵያ ፋውንዴሽን ጋር አብረን ለመስራት ተስማምተናል አሉ፡፡
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ የፋውንዴሽኑን መስራቾችና የበጎ ፍቃድ ቡድኑን በጽ/ቤታችን ተቀብለናቸዋል ብለዋል፡፡
የፋውንዴሽኑ የበጎ ፍቃድ ቡድን ለ5ኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከ700 በላይ የልብ ህሙማንን በማከም ከስቃይ አድኗል ነው ያሉት፡፡
በቀጣይም የህክምና ተራ እየጠበቁ ላሉ የልብ ህሙማን ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ ተቀናጅተን የብዙዎችን ሕይወት ለመታደግ በጋራ ለመስራት ተስማምተናል ብለዋል።
ፋውንዴሽኑ ትልቅ የህክምና ቡድን በማቀናጀት ህይወትን ለማዳን እያደረገ ያለውን ትጋት አድንቀው፥ በራሴና በታካሚዎች ስም አመሰግናለሁ ነው ያሉት፡፡