የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ችግኝ ለትውልድ የሚተላለፍ ተግባር ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ተፈጥሮአዊ ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም፣ የደን ሽፋንን ለማሳደግ እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ የቀረፀችው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአሁኑ ወቅት እምርታ እያስመዘገበ ይገኛል።
በዛሬው ዕለት የመገናኛ ብዙሃን ባስልጣን የሚዲያ ባለሙያዎችን ያሳተፈ የአረንጓዴ አሻራ አከናውኗል።
የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀይማኖት ዘለቀ እንዳሉት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የፖለቲካም ሆነ የልዩነት ድንበር የሌለው የጋራ ሀገራዊ አጀንዳ ነው።
መገናኛ ብዙሃን ይህንን አጀንዳ የህዝብ የዕለት ተዕለት ባህል እንዲሆን የማድረግ ሀላፊነት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ይህን ታላቅ ሀገራዊ እንቅስቃሴ ለህዝብ በማድረስ፣ ግንዛቤ በማስጨበጥ እና ህዝባዊ ንቅናቄውን በማጠናከር ረገድ የመገናኛ ብዙሃን የአንበሳውን ድርሻ ተወጥተዋል ብለዋል።
ይህ ሀገራዊ ስኬት እውን እንዲሆን ህዝባዊ ንቅናቄን በመፍጠር የድርሻውን መወጣቱን አስታውሰው፤ ባለስልጣኑ መገናኛ ብዙሃኑን በማስተባበር፣ መረጃዎች በፍጥነትና በጥራት ለህዝቡ እንዲደርሱ በማድረግ ረገድ ቁልፍ ሚና መጫወቱን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ያስመዘገበችው ስኬት የህዝብ ተሳትፎ፣ የመደመር መንግሥት ቁርጠኝነት እና የመገናኛ ብዙሃን ጥረት የተቀናጀ ውጤት ነው ብለዋል።
ይህንን ሀገራዊ እምርታ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ሚዲያው አሁንም የመሪነቱን ድርሻ ተወጥቶ ህዝቡን የማንቃት፣ የማስተማር እና የመከታተል ሀላፊነቱን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ነው ያሉት።
በዮሐንስ በቀለ