Fana: At a Speed of Life!

የገበታ ለትውልድ ፍሬ የሆነው የሸበሌ ሪዞርት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሸበሌ ሪዞርት የተፈጥሮ ውበትንና ባህላዊ እሴትን ከዘመናዊው አገልግሎት ጋር ያቀናጀ አዲስ የአፍሪካ የቱሪስት መስህብ ሆኗል።

የሸበሌ ሪዞርት መገንባት ለሶማሌ ክልል ብሎም ለምሥራቅ አፍሪካ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡

ፕሮጀክቱ የአካባቢውን የተፈጥሮ ድርቅና አስቸጋሪ የአየር ንብረት ወደ ለምለምና ማራኪ የቱሪስት መዳረሻነት መለወጥ እንደሚቻል በተግባር አሳይቷል።

ሪዞርቱ ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ፣ የጎረቤት ሀገራት መሪዎችንና ዓለም አቀፍ እንግዶችን በመሳብ ለቀጣናዊ ትስስርና ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅዖ እያበረከተ ይገኛል።

የሸበሌ ሪዞርት በሶማሌ ክልል በ385 ሄክታር ላይ የተገነባ ሲሆን፣ ጥር 23 ቀን 2018 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

ይህ የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት የቱሪዝም ዕድገትን፣ የባህል ልውውጥን እና ማህበራዊ ትስስርን ከማጠናከር አንጻር ትልቅ ሚና አለው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት በገበታ ለትውልድ መርሐ ግብር እውን የሆነው የሸበሌ ሪዞርት ከጅግጅጋ በ28 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ውብ ስፍራ ላይ ተገንብቷል።

ይህ በ385 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት፤ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ጸጋዎችና የሶማሌን ሕዝብ ባህላዊ ዕሴቶች በማስተሳሰር ሀገራችንን በአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ያለመ ታላቅ ፕሮጀክት ነው።

ሪዞርቱ 51 ዘመናዊ የመኝታ ክፍሎች፣ በአንድ ጊዜ እስከ 400 እንግዶችን ማስተናገድ የሚችሉ ሦስት ምግብ ቤቶች እና ዘመናዊ የስብሰባ አዳራሾችን በመያዙ ለአካባቢው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ባህልና ታሪክ በሚያንጸባርቅ መልኩ የተገነባ ሲሆን፣ በድርቅ ለሚታወቀው አካባቢ አዲስ ገፅታ በመስጠት 10 ሺህ የፍራፍሬ ተክሎችን እና የግመል ፓርክን በመያዙ የተፈጥሮን ውበት እየጠበቀ ይገኛል።

በፕሮጀክቱ የተገነቡት የ15 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገዶች እና የባህል ማዕከላት ማህበረሰቦች እንዲገናኙ፣ የሰላምና የአብሮነት እሴት እንዲጠናከር አድርገዋል።

የሸበሌ ሪዞርት የኢትዮጵያን የተደበቁ ጸጋዎች ለዓለም ማሳየት እንደሚቻል ያሳየ ድንቅ ስራ ነው።

ይህ የቱሪዝም ማዕከል የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ለትውልድ የሚተርፍ አዲስ የኩራትና የዕድገት ምልክት በመሆን ዘላቂ ፋይዳ ይኖረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.