የኢትዮጵያና አዘርባጃን የፓርላማ ትስስር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ያሳድጋል – አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 22፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የኢትዮጵያና አዘርባጃን የፓርላማ ትስስር የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ያሳድጋል አሉ።
አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ከአዘርባጃን ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሳሂባጋፋሮቫ (ዶ/ር) እና ልኡካቸው ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ አፈ ጉባኤው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በባኩ ያደረጉት ይፋዊ ጉብኝት በኢትዮጵያና አዘርባጃን ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ መክፈቱን አስታውሰዋል፡፡
ጉብኝቱ በፖለቲካ፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በኃይል፣ በቱሪዝም፣ በቴክኖሎጂና በሌሎች የጋራ ትኩረት በሚሹ ዘርፎች ያለውን ትብብር ለማሳደግ ጠንካራ መሠረት መጣሉን ገልጸዋል።
ሳሂባጋፋሮቫ (ዶ/ር) እና ልኡካቸው ያደረጉት ጉብኝት በሁለቱ ወዳጅ ሀገራት መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ የመጣውን ግንኙነት ወደ ተጨባጭ ለውጥ ለመቀየር ያለውን የጋራ ቁርጠኝነት የሚያሳይ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በ2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተካሄደው 3ኛው የኢትዮ-አዘርባጃን የፖለቲካ ምክክር መድረክ የሁለቱን ሀገራት የፖለቲካ ትስስር ወደ ከፍተኛ ደረጃ ማሳደጉን አንስተው፤ የዕውቀትና የልምድ ልውውጡ ተጠናከሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በተለይም አዘርባጃን ለኢትዮጵያ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማሻሻያ ያደረገችውን ድጋፍ በማድነቅ፤ ይህ ትብብር የመደመር መንግሥት አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመነ በሚያደርገው ጥረት ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላም የሀገራዊ ምክክር እያደረገች መሆኑን ገልፀው፤ ምክክሩ የሰላምና የብሔራዊ መግባባት ግንባታ ሂደትን ለማጠናከር ያለውን ሚና ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም ኢትዮጵያ ያደረገችውን ሀገራዊ ሪፎርም እንዲሁም የአረንጓዴ አሻራና የኮሪዶር ልማት ስራዎች በአካባቢ ጥበቃ፣ ዘላቂ ልማት እና የከተሞችን ዘመናዊነት በማፋጠን ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በፓርላማ ዲፕሎማሲ ዘርፍ የሁለቱ ሀገራት የወዳጅነት ቡድኖች በሕግ አወጣጥ፣ በተቋማዊ አቅም ግንባታ፣ በዲጂታል ፓርላማ ሥርዓት እንዲሁም የሕዝብ ተሳትፎን በማጎልበት ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ማሳደግ እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
በተለይ የወጣቶችና የሴቶች የፓርላማ አባላት ትስስር መጠናከር የሀገራቱን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እንደሚያሳድግ አመልክተዋል።
ሀገራቱ በፖለቲካ፣ በፓርላማ፣ በኢኮኖሚ፣ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም፣ በኃይል፣ በአየር ንብረት ለውጥ እና በሌሎች የጋራ ትኩረት ባላቸው ዘርፎች ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር የበለጠ ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆናቸው አረጋግጠዋል፡፡