8 ነጥብ 9 ሚሊየን ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) 8 ነጥብ 9 ሚሊየን ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆነዋል አሉ።
የትምህርት ሚኒስቴር አመራሮችና ሠራተኞች በ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምና በቀጣይ ዓመት እቅድ ውይይት ተካሂዷል።
ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በመድረኩ እንዳሉት፤ ትምህርት የሀገር ዕድገትም ሆነ ውድቀት ነጸብራቅ በመሆኑ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል።
ባለፉት 5 ዓመታት ለትምህርት ጥራት መሠረት የሚጥሉ ቁልፍ ተግባራት መከናወናቸውንም ገልፀው፤ ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች ግንባታና እድሳትን በአብነት አንስተዋል።
በተለይም ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በሁሉም ክልሎች የመገንባትና የማቋቋም ስራ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
የሁለተኛ ደረጃ መጽሐፍትን 1ለ1 ከማዳረስ በተጨማሪ ክልሎችን በመደገፍ የቅድመ አንደኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የመማሪያ መጽሐፍ በማሳተም ድጋፍ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
ዘጠኝ ዩኒቨርሲቲዎችን ወደ ራስ ገዝነት ለመሸጋገር በሚያስችል ሂደት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባላቸው ጸጋ መሠረት የመማር ማስተማር፣ ምርምር እና የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን እንዲሰጡ ስርዓት ተዘጋጅቶ እየተተገበረ መሆኑ ገልጸዋል።
ባለፉት 5 ዓመታት በተሰራው ስራ የተማሪዎች ምገባ አገልግሎት አቅም ማደጉን ጠቅሰው፤ አሁን ላይ ትምህርት ቤት ምገባ አቅም 8 ነጥብ 9 ሚሊየን መድረሱን ጠቁመዋል።
የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተናን ከኩረጃ እና ስርቆት ነጻ ለማድረግ በተሰራው ስራ በ2016 የተጀመረውን የበይነ መረብ ፈተና በዚህ ዓመት ከ62 በመቶ በላይ ማድረስ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በቀጣይ ሁሉም የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ተፈታኝ ተማሪዎች በበይነ መረብ እንዲፈተኑ እየተሰራ እንደሆነ መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።