Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ ከ157 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ አገኘ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት ሎጂስቲክስ በ2018 በጀት ዓመት 157 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ፡፡
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አብዱልበር ሸምሱ (ኢ/ር) በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ÷ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 7 ነጥብ 04 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ጭነት ማጓጓዝ ተችሏል፡፡
በዚህም 144 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 157 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል።
በአፈጻጸሙ የእቅዱን 108 ነጥብ 5 በመቶ ማሳካት የተቻለ ሲሆን ÷ ገቢው ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ27 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመልክተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከታክስ በፊት 28 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ትርፍ መገኘቱን ነው የገለጹት፡፡
ተቋሙ ከ20 ዓመት በኋላ ነዳጅን ለመጀመሪያ ጊዜ ማጓጓዙን የጠቀሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው÷ ይህም ከአጠቃላይ ጭነቶች ውስጥ የ1 ነጥብ 7 በመቶ ድርሻ እንዳለው አብራርተዋል፡፡
በዓመቱ 2 ሚሊየን ቶን የአፈር ማዳበሪያ የተጓጓዘ ሲሆን ÷ ከዚህ ውስጥም 74 በመቶው በተሽከርካሪ እና 26 በመቶው ደግሞ በባቡር መጓጓዙን አስረድተዋል፡፡
ለኤክስፖርተሮች 34 ሺህ ኮንቴይነሮች መቅረባቸውን ገልጸው÷ እስከ 2030 የሀገሪቱን የኮንቴይነር አቅርቦት 100 ሺህ ለማድረስ መታቀዱን አመልክተዋል፡፡
በመሳፍንት እያዩ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.