ኢትዮጵያ ሁለተኛ ቤታችን ናት – የአፍሪካ ቼዝ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአፍሪካ ቼዝ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በርናንድ ዋስዋ ዋንጃላን ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ሁለተኛ ቤታችን ናት አሉ፡፡
የአፍሪካ ቼዝ ኮንፌዴሬሽን 10ኛ ዓመታዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
በጉባዔው ኬኒያዊው በርናንድ ዋስዋ ዋንጃላን ኮንፌዴሬሽኑን ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ተመርጠዋል፡፡
የኮንፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት መቀመጫም በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ እንደሚሆን ተረጋግጧል፡፡
በርናንድ ዋስዋ ዋንጃላን በዚህ ወቅት ÷ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ ቼዝ ስፖርት እድገት የአፍሪካ ቼዝ ኮንፌዴሬሽን ጽ/ቤቱን በአዲስ አበባ በቅርቡ በመክፈት ወደ ሥራ እንገባለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን ሁለተኛ ቤታችን ናት ሲሉም ነው የገለጹት፡፡
አዲስ አበባ ከተማ በአፍሪካ ካሉ ውብ ከተሞች መካከል አንዷ ናት፤ ለአዲስ አበባ ከተማ ውብ ገጽታ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቼዝ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ተሾመ በቀለ በበኩላቸው÷ኢትዮጵያ ውድድሮችን እና ጉባዔዎችን ማዘጋጀቷ በተለያየ መልኩ ተጠቃሚ ያደርጋታል ብለዋል፡፡
የኮንፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት በአዲስ አበባ ሲከፈት ለተለያዩ ሰዎች የሥራ እድል እንደሚፈጥር አስገንዝበዋል፡፡
በእንዳልካቸው ወዳጄ