አረንጓዴ ዐሻራ የአካባቢ ጥበቃ ሥራን በማጠናከር ምርታማነትን እያሳደገ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የመደመር መንግሥት እሳቤ የሆነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የአካባቢ ጥበቃ ሥራን በማጠናከር ምርታማነትን እያሳደገ ነው አሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በምሥራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ኢላላ ቀበሌ አረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።
አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ባለፉት ዓመታት የመደመር መንግሥት በትኩረት ከሰራባቸው ጉዳዮች መካከል የአካባቢ ጥበቃ ሥራ አንዱ ነው፡፡
በዚህም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ተጨባጭ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዓመታት ከ28 ቢሊየን በላይ ችግኝ መተከሉን ጠቁመው ÷ በዚህም 17 በመቶ የነበረው የደን ሽፋን ወደ 29 በመቶ በላይ ማደጉን አንስተዋል፡፡
በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በተከናወነ ሥራ በአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
መርሐ ግብሩ ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ጥረት እውን ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ነው ያመላከቱት፡፡
በኦሮሚያ ክልል በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር በሁሉም አካባቢዎች ነዋሪዎች በነቂስ ወጥተው እየተሳተፉ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ