ያለፉት ዓመታት የምናልመው ሁሉ እውን የሆኑባቸው ዓመታት ናቸው – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር የምናልመው ሁሉ እውን የሆኑባቸው ዓመታት ናቸው አሉ፡፡
ፕሬዚዳንቱ በዛሬው ዕለት እየተካሄደ በሚገኘው የአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ዐሻራቸውን አኑረዋል።
በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በ2011 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በኢትዮጵያ በርካታ ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ጫካዎች፣ አዝዕርቶች፣ አትክልቶች፣ በተፈጥሮ ጸጋ የተቸሩን ናቸው ያሉት ፕሬዚዳንት ታዬ፤ ተፈጥሮ በሰጠን ልክ የማልማት ተነሳሽነታችን እጅግ አናሳ ነበር ብለዋል።
በዚህም ብዙ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን አጥተናል በማለት ጠቅሰው፤ በዚህም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዝ በርካታ ጉዳቶችን አስተናግደናል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ለድርቅ ስትጋለጥ መኖሯን በማንሳት ይህንን ታሪክ ለመቀየር ከተወጠኑት ውጥኖች መካከል አንደኛው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በየዓመቱ ዜጎችን በማስተባበር የተጀመረው ይህ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር ለዚህ ትወልድ ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ትውድ ትሩፋት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በቢሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ኢትዮጵያውያን ታሪክ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
መርሐ ግብሩ ከሀገራት ጋር ሲነጻጸር የተወሰኑ ሀገራት ብቻ እንደ ህዝብ በጋራ ችግኝ የመትከል ልምድ እንዳላቸው በመጥቀስ ሆኖም ከኢትዮጵያ ጋር የሚነጻጻር የችግኝ ቁጥር እንደማይተከል ጠቁመዋል፡፡
የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ትልምን ጨምሮ ባለፉት ዓመታት በመደመር መንግሥት የታቀዱ ተግባራት እውን እየሆኑ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
በአቤል ነዋይ