የግብፅ የሀሰት ትርክት እና የኢትዮጵያ እውነታዎች
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 29፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ግብፅ የአረብ ሀገራትን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለሕዳሴ ግድ የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖረው ለማድረግ የምታደርገውን ሙከራ ተከታትላ እያከሸፈች ትገኛለች፡፡
ግብፅ ኢትዮጵያን በዓባይ ወንዝ ባላት ውሃ አጠቃቀም መብት፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እንዲሁም በቀይ ባህርና በአፍሪካ ቀንድ ባላት የጂኦፖለቲካ ተጽዕኖ ምክንያት ለዘመናት እንደ ስጋት ስትቆጥራት ቆይታለች፡፡
በተለይም የዓባይ ወንዝን በብቸኝነት ለመጠቀም ባላት ፍላጎት ከቅኝ ግዛት ዘመን ጀምሮ የነበሩ ስምምነቶች በማጣቀስ ፍትሐዊ አጠቃቀምን ስትገፋ ኖራለች።
ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እና የአስተዳደር ስርዓት የውሃ መጠኔን ይቀንስብኛል፣ አልፎ አልፎ ደግሞ ግድቡ የተፋሰሱ ሀገራት የጎርፍ አደጋ እያደረሰ ነው በሚል የሚጣረሱ ክሶችን በተደጋጋሚ አቅርባለች።
ይህ ብቻ አይደለም። የቀጣናው ሀገራትን በተለያየ መንገድ በመደለል፣ የውስጥ ባንዳዎችን በመሳሪያነት በመጠቀም ኢትዮጵያ ከባሕር በር ማዕድ ተቋዳሽ እንዳትሆን እየሰራች ነው።
ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድቡን እውን ስታደርግ የታችኛውን ተፋሰስ ሀገራት ጭምር በማድረግ ፍትሐዊ የሆነ የተጠቃሚነትን መርህ ይዛ ነው። ይህ አቋሟ የጸና መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይታለች።
ኢትዮጵያ የምታራምደውን ፍትሃዊ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ዓለም የተረዳው ሲሆን፤ ከግብፅ መሰረተ ቢስ ውንጀላዎች ይልቅ የኢትዮጵያን እውነቶችን እየተረዳ ይገኛል፡፡
የግብጽ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ፣ በዓባይ ወንዝ እና በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ለአረቡ ዓለም እና ለዲፕሎማሲው ማህበረሰብ የተሳሳተ ትርክት ቢያቀርቡም ኢትዮጵያ እውነቱን በመግለጥ የግብፅን ሴራ እያከሸፈች ትገኛለች፡፡
የግብፅን ሴራ ለማክሸፍ እና የሀገርን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውም ማጠናከር፣ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን በስክነት መምራት፣ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንዲሁም የጋራ አቋም መያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ከጎረቤት ሀገራት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠር፣ የዓባይን ወንዝ በፍትሃዊነት መጠቀምን ለዓለም ማሳወቅ እንዲሁም የተዛባ መረጃን ተከታትሎ ማጋለጥ ደግሞ ከሁሉም ኢትዮጵያውያን እና ከመደመር መንግሥት የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
በሚኪያስ አየለ