ምክክሩ ለኢትዮጵያ ችግሮች ኢትዮጵያዊ መፍትሔ የሚያበጅ ነው – ተመካካሪዎች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ለሀገሪቱ የረጅም ጊዜ ችግሮች ኢትዮጵያዊ የሆነ ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት የሚያስችል ታሪካዊ መድረክ ነው አሉ ተመካካሪዎች።
የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄዱን ቀጥሏል።
ኢትዮጵያውያንን የሚወክሉ 4 ሺህ የሕዝብ ወኪሎችም በስምንት ዐበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር ጥልቅና አሳታፊ ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ።
ተመካካሪዎች በግልጽነት መንፈስ የሚያደርጓቸው ጥልቅ ውይይቶች ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጉዞ እና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት እንደሚጥሉ ይታመናል።
ተመካካሪዎች እንዳሉት፤ ምክክሩ የጋራ መግባባትን በማጠናከር እና ልዩነቶችን በምክክር ለመፍታት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።
ከተመካካሪዎች መካከል አባ ገዳ ተሾመ በቀለ፤ ሀገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ምዕራፍ የሚያሻግርና በዜጎች መካከል ያለውን ትስስር የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ምክክሩ ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን ለማስረከብ ዕድል የሚፈጥር ሲሆን፣ ይህም ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን አንስተዋል።
በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር ተሰባስበን የምናካሂደው እንደመሆኑ መጠን ልዩ ልዩ ሐሳቦች የሚስተናገዱት በመከባበር እና በመደማመጥ መንፈስ ነው ብለዋል።
ይህ በታሪካችን ተደርጎ የማይታወቅ እና የዘገየ ቢሆንም በእኛ ዘመን ለሀገራችን ዘላቂ መፍትሔ ይዞ እንደሚመጣ ትልቅ ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ሌላኛዋ ተመካካሪ ነፃነት ሲሳይ በበኩላቸው፣ እጅግ አሳታፊ በሆነው በዚህ የምክክር መድረክ ሁሉም ተመካካሪዎች በንቃት በመሳተፍ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የሐሳብ ልዩነቶች ተፈጥሮአዊ መሆናቸውን በማንሳት አለመግባባቶችን በምክክር መፍታት ለቀጣይ ትውልድ የምትሆን ሀገር ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን ለኢዜ ተናግረዋል።
ለዚህም አሁን እየተካሄደ ያለው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ዘላቂ ሰላምን እና አብሮነትን ለማረጋገጥ የሚረዳ መልካም አጋጣሚ ነው ብለዋል።
ሀገራዊ የምክክር መድረኩ በሀገር ሰላምና ልማት ጉዳዮች ላይ በመምከር የተሻለች ሀገር ለመገንባት የሚያስችል ነው ያሉት ደግሞ ተመካካሪ ዱናሞ ኡሞጎ ናቸው፡፡
በምክክሩ ላይ ለኢትዮጵያ ችግሮች እውነተኛ መፍትሔ ለማምጣት የሚያስችሉ ትክክለኛ ሐሳቦችን ማንጸባረቅ የተቻለበት ነው ብለዋል።
ተመካካሪ ተሰማ ላንዴቦ ፣ ሀገራዊ ምክክሩ ሁሉንም ያሳተፈ በመሆኑ ለሀገሪቱ ተጨባጭ የመፍትሔ ሐሳቦችን የሚያፈልቅ እንደሚሆን ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
የሀሳብ እና የመናገር ነጻነት በስፋት የሚንጸባረቅበት መድረክ መሆኑን ነው ያመላከቱት፡፡