ሲንቄ ባንክ የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ ያስመዘገበው ስኬት በአርአያነት የሚጠቀስ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሲንቄ ባንክ የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥ ረገድ ያስመዘገበው ስኬት በአርአያነት የሚጠቀስ ነው አሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ፡፡
የሲንቄ ባንክ የ2025/26 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ በዚህ ወቅት÷ሲንቄ ባንክ በ2025/26 በጀት ዓመት ያስመዘገበውን አፈጻጸም እጅግ ከፍተኛ ነው ሲሉ አድንቀዋል፡፡
ባንኩ የፋይናንስ አካታችነትን በማረጋገጥና የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ በማሳደግ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚ እና ልማት ላይ ያከናወናው ተግባር በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል፡፡
ባንኩ እስካሁን ለኢኮኖሚው ያቀረበው ጠቅላላ ብድር የማሕበረሰቡን ሕይወት በቀጥታ በመለወጥና የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ያለው ትርጉም እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ያመላክታል ነው ያሉት፡፡
ባንኩ የጀመረውን ሁለንተናዊ የዕድገት ጉዞ አጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት ንዋይ መገርሳ በበኩላቸው ÷ ባንኩ ባለፈው የበጀት ዓመት ያስመዘገበው ውጤት እጅግ ከፍተኛ እና ሁለንተናዊ ጉዞውን የሚያፋጥን መሆኑን ገልጸዋል።
ባንኩ እስካሁን ለኢኮኖሚው ያቀረበው ጠቅላላ የብድር መጠን 127 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር የደረሰ ሲሆን÷ በዚህም ከ855 ሺህ በላይ ዜጎችን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል፡፡
የሲንቄ ባንክ ጠቅላላ ሀብት መጠን 216 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር መድረሱንም ነው የገለጹት፡፡