የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2018 በጀት ዓመት 36 ነጥብ 08 ቢሊየን ብር ግብር ከፈለ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2018 በጀት ዓመት 36 ነጥብ 08 ቢሊየን ብር ግብር ከፈለ፡፡
ለሀገር የሚከፈል ግብር፤ ለትውልድ የሚተላለፍ ሀብት ነው የሚለው ባንኩ ግብርን በታማኝነት መክፈል የሀገርን ልማት መደገፍ መሆኑን ጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፋይናንስ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ በታማኝነት እና በኃላፊነት የግብር ግዴታውን በመወጣት አርአያነቱን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።
ተቋሙ በ2018 በጀት ዓመት ብቻ 36 ነጥብ 08 ቢሊየን ብር ግብር በመክፈል ለኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት የራሱን የላቀ አሻራ ማሳረፍ መቻሉን ከባንኩ የተገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2018 በጀት ዓመት 707 ነጥብ 47 ቢሊየን ብር ሀብት በማሰባሰብ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘቡን ከ2 ነጥብ 4 ትሪሊየን ብር በላይ ማድረሱ የሚታወስ ነው።
የሀብት አሰባሰብ ተግባሩ በ2017 በጀት ዓመት ከነበረው ተቀማጭ የ37 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን ባንኩ መግለጹ አይዘነጋም፡፡