የሳዑዲ ተመላሾችን ክብራቸው ተጠብቆ ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ በትኩረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሳዑዲ ዓረቢያ ስደት ተመላሽ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ መብትና ክብራቸው ተጠብቆ ወደ ቤተሰቦቻቸው የማቀላቀሉ ሥራ በተቀናጀ ሁኔታ እየተከናወነ ነው አለ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፡፡
ኮሚሽኑ ከሳዑዲ ዓረቢያው ንጉሥ ሳልማን የሰብዓዊ እርዳታ ማዕከል ጋር በመተባበር ከስደት ተመላሾችን መልሶ ማቋቋም የሚያስችል የድጋፍ ስምምነት ተፈራርሟል።
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የዜጎችን ክብርና ደህንነት ማዕከል ያደረገ የዲፕሎማሲ ትብብር ውጤት እያስመዘገበ ነው፡፡
ከሳዑዲ ዓረቢያ የሚመለሱ ዜጎችን በክብርና በደህንነት መቀበልና መደገፍ የመንግሥትን ዜጋ ተኮር አስተዳደር አቅጣጫ የሚያሳይ ተግባራዊ ሥራ ነው ብለዋል፡፡
ሰብዓዊ ድጋፍን ይበልጥ ለማሳደግ ከልማት አጋር ተቋማት ጋር የሚደረገው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡
ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ተቋማትና ከኪንግ ሳልማን የሰብዓዊ ድጋፍና የዕርዳታ ማዕከል ጋር የተጀመረው ትብብር ወደ ዘላቂ የልማትና የሰብዓዊ ድጋፍ አጋርነት እየተሸጋገረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዚህ የትብብር ማዕቀፍ የኪንግ ሳልማን የሰብዓዊ ድጋፍና የዕርዳታ ማዕከል ለተመላሽ ዜጎች የሚውል 1 ነጥብ 333 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ማድረጉ ተመላክቷል፡፡
ድጋፉ በኮሚሽኑ በአደጋ ጊዜ ድጋፍ ፕሮጀክት ሥር እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን÷ በዚህም ተመላሾች ወደ ቤተሰቦቻቸ በክብርና በደህንነት እንዲደርሱ ለመጓጓዣ፣ ለምግብ፣ ለመጠለያ፣ ለአልባሳትና ሌሎች ድጋፎች እየዋለ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሳዑዲ ዓረቢያ አምባሳደር አብዱላህ ሀሰን አልዛህራኒ በበኩላቸው ÷ የኢትዮጵያና የሳዑዲ ዓረቢያ ታሪካዊ አጋርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ማለታቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡