Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል በበልግ ከለማው መሬት ከ21 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ተሰበሰበ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 8፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው የበልግ እርሻ በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ እስካሁን ከ21 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብሰቧል አለ የክልሉ ግብርና ቢሮ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ እንደገለጹት÷ በክልሉ በበልግ ወቅት ወደ 2 ሚሊየን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በተለያዩ የሰብል ዓይነቶች ለምቶ ወደ ምርት መሰብሰብ ተገብቷል።
ለበልግ እርሻው ውጤታማነት ለአርሶ አደሩ የሙያ ብቃትን የሚያሳድጉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች የተሰጡ ሲሆን÷ ባለሙያዎች በመስክ በመገኘት ያልተቋረጠ ሙያዊ ድጋፍና ክትትል ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።
ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ የግብርና ግብዓቶች በወቅቱ ለአርሶ አደሩ እንዲደርሱ መደረጉን ጠቁመው÷ ከዚህ በተጨማሪም ሰብሉን ከተባይና ከአረም ለመጠበቅ የሚያስችሉ የፀረ ተባይና የፀረ አረም መድሃኒቶች አቅርቦት መመቻቸቱን ገልጸዋል።
በኦሮሚያ ክልል የበልግ እርሻ ልማት ለአርሶና አርብቶ አደሩ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ምንጭና የምግብ ዋስትና መሰረት መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
በክልሉ በበልግ ዝናብ የሚከናወነው ይህ የግብርና እንቅስቃሴ አርሶ አደሩ የምግብ ፍላጎቱን እንዲሸፍን ከማስቻሉም በላይ፣ ገበያን ለማረጋጋት የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
በተለይም እንደ ቦረና፣ ጉጂና አርሲ ባሉ አካባቢዎች በበልግ እርሻው የከብት መኖን ከማልማት ባሻገር ዋና ዋና የህብረተሰቡ የፍጆታ ሰብሎች የሚመረቱበት በመሆኑ ለክልሉ ግብርና መነቃቃት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ኢዜአ ዘግቧል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.