Fana: At a Speed of Life!

የሀገር ሉዓላዊነትና የልማት ዘብ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገርን ሉዓላዊነትና የሕዝብን ደህንነት የመጠበቅ ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት የተጣለበት የሰላምና የአይነኬነት አምድ ነው፡፡

የሰራዊቱ ሚና ዳር ድንበርን ከማስከበርና ሰላምን ከመጠበቅ ባሻገር ለሀገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ እድገትና የብልጽግና ጉዞ የሚያደርገው አስተዋፅኦ ጉልህ ነው።

ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ እድገትና ብልጽግና ያለ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ ሊታሰብ አይችልም።

ሰራዊቱ ውስጣዊና ውጫዊ የሰላምና ደህንነት ስጋቶችን በመከላከል የኢንቨስትመንትና የልማት እንቅስቃሴዎች በነፃነት እንዲካሄዱ አስተማማኝ ከባቢ ይፈጥራል።

ይህ የሰላም ዋስትና የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በልማት ስራዎች ላይ በነፃነት እንዲሳተፉ መንገድ ይከፍታል።

ከዚህ ባለፈ መከላከያ ሰራዊቱ በሀገሪቱ ዋና ዋና የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ረገድ ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል።

ሰራዊቱ በስሩ ባሉ የኢንጂነሪንግና የቴክኖሎጂ ተቋማት አማካኝነት ድልድዮችን፣ መንገዶችንና ግድቦችን ጨምሮ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን በመገንባት ከድንበር ጋሻነት ጎን ለጎን በልማት ዘመቻዎችም የሀገር መከታነቱን እያስመሰከረ ነው፡፡

የመከላከያ ተቋማት ወታደራዊ ቁሳቁሶችን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት የቴክኖሎጂና የኢንዱስትሪ አቅማውን በማሳደግ ላይ ይገኛሉ።

በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በፈጠራ ስራዎችና በሀገር ውስጥ ምርቶች እድገት ላይ የሚያሳድሩት በጎ ተጽእኖ የሀገር ውስጥ ገበያን ለማጠናከርና የውጭ ምንዛሪን ከፍተኛ ወጪ ለማዳን ይረዳል።

ሰራዊቱ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን በማሰልጠን ብቁና አምራች ዜጋን በማፍራት ረገድ የማይተካ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ይህም በየጊዜው ወደ ሲቪል ህይወት የሚቀላቀሉ አባላት በየተሰማሩበት የልማት ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ ያስችላል፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የሀገርን ዳር ድንበር፣ ሰላምና ደህንነት ከመጠበቅ ባለፈ ለዘላቂ ልማትና የብልጽግና ጉዞ ከፍተኛ ድርሻን በመወጣት ላይ የሚገኝ የሀገር አለኝታ ነው።

በመልካም ፈቃዱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.