አጀንዳዎችን የማጣጣም ሥራ ሲያከናውኑ የነበሩ ተወካዮች ለሥራ ቡድናቸው አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 11፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከስምንቱ የሥራ ቡድኖች የተውጣጡ 15 የአጀንዳ ምክረ ሃሳብ አጠናቃሪዎች ያጠናቀሩትን የአጀንዳ ሃሳብ ለየሥራ ቡድናቸው አቅርበዋል አለ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን::
500 አባላት ካሏቸው ስምንት የስራ ቡድኖች ከእያንዳንዳቸው 15፣ በድምሩ 120 አባላት ያሉት ቡድን ካለፈው ሐሙስ ነሐሴ 7 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የሥራ ቡድኖች የተነሱ የአጀንዳ ምክረ ሃሳቦችን በማዳመጥ ወጥ የሆነ ምክረ ሃሳብ ማቅረብ የሚያስችል ሥራ ሲያከናውን ቆይቷል።
የእያንዳንዱ የሥራ ቡድን ተወካዮችም የየቡድናቸውን የአጀንዳ ምክረ-ሃሳቦች ድግግሞሽ በማስወገድ፣ ያልተቀናጁ ሀሳቦችን በማደራጀት ወጥ የሆነ ሰነድ አዘጋጅተው ዛሬ ነሐሴ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ 500 አባላት ላሉት የሥራ ቡድን አቅርበዋል፡፡
የተደራጁ አጀንዳዎች የቀረቡላቸው ስምንቱ የሥራ ቡድኖች ሃሳብ እና አስተያየት አክለው የመጨረሻው ሰነድ እንዲዘጋጅ ለአደራጅ ቡድኖቹ መልሰዋል፡፡
የአጀንዳ ምክረ-ሃሳቦችን የሚያጣጥሙ ቡድኖችም የተሰጧቸውን ሃሳቦች በነገው ጠዋት መርሐ ግብር አካትተው ለየሥራ ቡድኖቻቸው በከሰዓቱ መርሐ ግብር በድጋሚ በማቅረብ ያጸድቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡